ቀጥታ፡

"እኔ ብቻ ነኝ የተበደልኩ" የሚለው ክስ ዛሬም ከተበዳይነት ትርክት አለመውጣታችን ማሳያ ነው - የአገር ሽማግሌዎች መማክርት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ "እኔ ብቻ ነኝ የተበደልኩ" የሚለው ክስ ዛሬም ከተበዳይነት ትርክት አለመውጣታችን ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ገለጸ።

መማክርቱ ብልፅግና ፓርቲና ሕወሓት በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውናል ብሏል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን አለመግባባት ለማሸማገል ወደ ትግራይ ክልል አቅንቶ የነበረው መማክርት በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት፤ ፓርቲዎቹ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የአገር ሽማግሌዎች ማሸማገል ጀምረዋል።

የአገር ሽማግሌዎች ወደ ትግራይ ክልል በሄድንበት ወቅት ከክልሉ መሪዎች ''ኃይለኛ'' የተበዳይነት ስሜት እንዳለ ተረድተናል ብለዋል።

"ኢሕአዴግ እያለ በጋራ ሆነው አድራጊ ፈጣሪ የነበሩ ሰዎች ናቸው። ዛሬ ተበዳይ ሆነው የቀረቡ መቼ ይሆን ለንስሐ የምንናገረው?" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ፓርቲዎች ከተበዳይነት ትርክት ወጥተው እነሱም በዳይ ሊሆኑ ስለሚችሉ ወደ ራሳቸው ማየት እንደሚገባቸው ፕሮፌሰር መስፍን አሳስበዋል።

የመማክርቱ ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በተለያዩ አካባቢዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት በሕዝቡ መካከል ችግር እንደሌለ አረጋግጠውልናል ብሏል።

ሁለቱን አካላት  ስንነጋገርም ተቀራርቦ አለመነጋገር እንጂ፤ ሌላ የጎላ ችግር እንዳላገኙ ገልጿል።

ሌላኛው የመማክርቱ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ ሁለቱም ፓርቲዎች ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው መሬ መሠረት የሌለው ተራ አሉባልታ መሆኑን ገልጸዋል።

መማክርቱ ወደ ትግራይ ክልል ያቀናው በዚህ ሣምንት ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም