ኮሚሽኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በመጪው ክረምት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ከነዚህም 434ሺህ 154 የሚሆኑት ለከፋ ችግርና መፈናቀልእንደሚዳረጉም ተመልክቷል።
በኮሚሽኑ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ የኮሚሽኑ የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ ኃይል ያደረገው ምልከታ፤ ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ለይቷል ብለዋል።
አደጋው በሁሉም ክልሎች የሚከሰት ሲሆን፣ የሚያደርሰው ጉዳት ግን እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚለያይ አስረድተዋል።
በተያዘው ዓመት በበልግ ወራት በተከሰተው ጎርፍ አደጋ ከ300ሺህ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉና ከ400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ወይዘሮ አልማዝ አስታውሰዋል።
አደጋው በክረምቱ ወቅት የከፋ ስለሚሆን በማሣ ላይ ውኃ እንዳያቁር፣ የጎርፍ መፋሰሻዎችንና መንገዶች እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ጉዳት የሚደርሰባቸውን ዜጎች ለመርዳት ከክልሎችና ከብሔራዊ ሜትሪዎሮሎጂ ኤጀንሲ በተገኘ መረጃ መሠረት ድጋፍ ለሚሰጡ ድርጅቶችና ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እንዲደርስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ጥናትና ትግበራ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒሩት ሽፈራው በበኩላቸው በከተማዋ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከልና ለመቀነስ 261 ቦታዎች ተለይተው በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ አካባቢውን በማጽዳትና የተደፈኑ ቱቦዎችንም በመክፈት አደጋ የመከላከል ባህሉን ማሳደግ አለበት ብለዋል፡፡
ከኅብረተሰቡ አቅም በላይ የሆኑ አደጋዎች ከተፈጠሩ በተዘጋጁት መሣሪያዎችና ባለሙያዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ወይዘሮ ሒሩት ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች አቶ አቤል ገረመው የጎርፍ አደጋን ለመከላክልና ለመቀነስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሚያደርሰው ጉዳት አንጻር ሲታይ ግን በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
በከተማዋ የተወሰኑ አካባቢዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች የሚደረገው ድጋፍ ማነስ፤ በወንዝ ዳርቻ የሰፈሩና በመሬት መደርመስ ጉዳት የሚደርስባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን የማንሳት ሥራ ዝቅተኛ መሆኑን ነዋሪዎች ሲገልጹ ይሰማል።