ቀጥታ፡

ተጨማሪ 116 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ 7 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4809 የላብራቶሪ ምርመራ 116 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ 7 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4ሺህ 70 ደርሷል፡፡

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 76 ወንድና 40 ሴት እንዲሁም የዕድሜ ክልላቸው ከ3 እስክ 78 አመት እንደሆነ ታውቋል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 101 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ 6 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ 1 ሰው ከአፋር ክልል፣ 1 ሰው ከትግራይ ክልል፣ 1 ሰው ከአማራ ክልል ፣ 1 ሰው ከጋምቤላ ክልል እንዲሁም 1 ሰው ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የ 7 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን 5ቱ በህክምና ማዕከል ሲረዱ የነበሩ፣ 1 ደግሞ ሰው በጤና ተቋም ላይ የነበሩ እንዲሁም 1 ሰው በአስከሬን ምርመራ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈ መሆኑ ታውቋል።

በዚህም አጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 72 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዜጎች ሞት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 93 ሰዎች ( 88 ከአዲስ አበባ፣ 2 ከሱማሌ ክልል፣ 1 ከኦሮሚያ ክልል፣ እና 2 ከአማራ ክልል ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1027 መድረሱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በጽኑ ህክምና ክትትል የሚደረግላቸው 32 ሰዎች ናቸውም ተብሏል።

እስካሁን በአገራችን አጠቃላይ 207 ሺህ 023 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም