የኢትዮ- ቻይና ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድጓል -ኢኒሼቲቩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ- ቻይና ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድጓል -ኢኒሼቲቩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) የኢትዮ - ቻይና ትብብር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን ቤልት ኤንድሮድ ኢኒሼቲቭ አስታወቀ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ትብብር ወደ አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩን አመልክቷል።
አገሮቹ ከወረርሽኙ በኋላ ያስተናገዱት ዘርፈ ብዙ ኩነት ትብብራቸው እያደገ ለመምጣቱ እውን ምስክር መሆኑን ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ በቪዲዮ በተደረገው በቻይና-አፍሪካ ትብብር ላይ "በዚህ ለመተንበይ በሚያዳግት ጊዜ፣ በአፍሪካ አገሮችና በቻይና መካከል የታየው በአንድነት መቆም ዓይነተኛ እሴት ነው'' ብለዋል፡፡
በቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም ወቅት ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ያነሷቸውን ስምንት ዐበይት እንቅስቃሴዎች በማስታወስ፣ ለጤና አገልግሎት ቅድሚያና ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ከሁለት ወራት በፊት አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁስ ጋር አዲስ አበባ ያደረሱት የቻይና ዘመናዊና ባህላዊ የሕክምና ባለሙያዎች ለፈጣን ምላሹ ዋና ማሳያ ተደርገው ይቆጠራሉ።
ባለሙያዎቹ ወረርሸኙ ከተከሰተ በኋላ ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የላከችው ቀዳሚ ቡድን አባላት ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ ምስጋና የቸረችውና “ሁለንተናዊ ትብብርን ያሳየ” ተግባር ነበር ብሏል ኢኒሼቲቩ።
በኢትዮጵያ የሁለት ሳምንት ቆይታ ያደረጉት ባለሙያዎቹ ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች፣ የጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ኢንስቲቲዩት ኃላፊዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።
የኢትዮጵያን ወረርሸኝ መከላከል ስትራቴጂን በሚያድግበት መንገድ ላይም መምከራቸውን ጽፏል።
በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት የሚያግዙ በርካታ የቻይና መንግሥታዊ ተቋማትና የግል ኩባንያዎች የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ለግሰዋል።
በቻይና ድጋፍ የተቋቋመው የሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ላይ አተኩሮ እየሰራ ሲሆን፤ በመንግሥት ጥያቄ ሕሙማንን በማከም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በመንግሥታቱ አድናቆት ተሰጥቶታል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና የኦሽኒያ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዳዊት ይርጋ “የአፍሪካ ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከመቼውም ጊዜ በላቀ እድገት አሳይቷል” ብለዋል።
በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የትብብሩ ጠቃሚነትና እድገት በግልፅ መታየቱን መስክረዋል።
“አፍሪካና ቻይና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጠንካራ አጋር ናቸው።የሲኖ-አፍሪካ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጥንካሬ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በሚገባ ታይቷል “ በማለት ተናግረዋል።
“በአፍሪካ ቻይና ትብብር ውስጥ ህብረት ጠንካራ መሠረት መሆኑ ታይቷል።
የኮቪድ-19 ወረርሸኝ በቻይና በተከሰተበት ወቅት አፍሪካ ከቻይና ጎን በጽናት ቆማለች።
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በጽናት ከጎናችን በመቆም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት የሚያግዝ ድጋፏን በመስጠቷ ከልብ እናመሰግናለን “ በማለት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመግታት የተደረገውን ትብብርና አጋርነት አድንቀዋል።
“እንደ አፍሪካዊ አፍሪካን በመወከል ቻይና በቅን ልቦና የኮቪድ-19 ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ በማድረጓ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ “ብለዋል።
“ድጋፉ ሕይወት አድን የህክምና ቁሳቁስን የያዘ ነው። ፍጥነት ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ነው አፍሪካውያን ደግሞ ድጋፉን በፍጥነት ይፈልጉታል “ በማለት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ድጋፉን በፍጥነት በሟጓጓዝ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ማሳረፉም ተገልጿል።
“አፍሪካ ቻይናን ፤ቻይና ደግሞ አፍሪካን ትፈልጋለች። እኛም በጋራ በመሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እንዋጋለን “በማለት የአጋርነቱን ጥልቀት አመላክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ የቻይና መንግሥትና ጃክ ማን የመሰሉ ባለሀብቶች የሚያደርጉት ድጋፍ እንደሚጠናከር እምነታቸውን ገልጸዋል።