ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት በትግራይ ጥሩ ቆይታ እንደነበረው ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2012(ኢዜአ) በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግስት መካከል የሚስተዋለውን አለመግባባት ለመፍታት ወደ መቀሌ አቅንተው የነበሩ የሃገር ሽማግሌዎች ጥሩ ቆይታ እንደነበራቸው የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ገለጸ።

የሽምግልናውን የመቀሌ ቆይታ በሚመለከት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው አሉታዊ ወሬም ትክክል አይደለም ተብሏል።

በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ለሁለቱም ወገኖች ጥያቄ ማቅረቡን የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ገልጿል።

የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እና ምክትል ሰብሳቢዎች ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም ሽምግልናው በክልሉና በፌዴራል መንግስት መካከል ያለውን ፖለቲካዊ አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ለማቀራረብ ነው ብለዋል፡፡

የሽምግልና ሂደቱ የተጀመረው ቀደም ብሎ እንደነበር ገልፀው ኮቪድ 19 እና እሱን ተከትሎ መንግሥት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳዘገየውም ገልጸዋል።

ነገር ግን ሂደቱ ተካርሮ ችግር ከሚፈጠር ቀድሞ መፍትሔ እንድበጅለት ለማወያየት ወደ መቀሌ ማቅናታቸውን ገልጸዋል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ በመግለጫው "ከሁለቱም ወገን ችግር የለም፤ ችግሩ ተቀራርቦ አለመወያየት ብቻ ነው" ብለዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎቹ ወደ ትግራይ ባቀኑበት ወቅት የክልሉ ህዝብና መንግስት በአግባቡ ተቀብሎ እንዳስተናገዳቸው ተናግረው፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአሉታዊ መልኩ የሚሰራጨው ወሬ እውነታ የሌለው መሆኑንም አብራርተዋል።

ለሽምግልና ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው የነበሩ 43 የሃገር ሽማግሌዎች ጥሩ ቆይታ እንደነበራቸውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም