ቀጥታ፡

ግብፅ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር ብቻ ነው...ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) ዛሬም ሆነ ወደፊትም ግብፅ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር ብቻ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የአባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪና ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ለግብፅ ሌላ አማራጭ ማማተር ከንቱ ነው፡፡

ግብፅ፣ ሱዳን ወይም የትኛውም ሌላ ወገን ማወቅ ያለበት እ.ኤ.አ ከ2015 የመርህ መግለጫ ሰነድ በስተቀር ኢትዮጵያ ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር አስገዳጅ ውለታ እንደሌላት ነው፡፡

‹‹በአባይ ውሃ የኢትዮጵያ መብት፣ ከግብፅ የተረፈ መሆን የለበትም›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ከሆነማ ኢትዮጵያ የውሃ መብት ሉዓላዊ ባለቤትነት አይኖራትም ማለት ነው›› ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ እስከዛሬም ድረስ ግብፅ የምትሄድበት አካሄድ የማይገባት አካሄድ መሆኑ መታወቅ አለበት።

የአባይ ውሃ ከኢትዮጵያ ይነሳል ያሉት ፕሮፌሰሩ ፤ ‹‹ለወደፊቱም እንዲሁ ይቀጥላል። ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ስለሆነ በመተሳሰብና በመተባበር በውሃ ሀብቱ ሁሉም መጠቀም ይችላል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ስለዚህም የግብፅ ፍላጎት የሌሎች ውሃ ተጋሪዎች ጥቅም፣ መብትና የልማት ፍላጎት ሊረመርም አይገባም፤ አይችልምም።

ምንጊዜም ቢሆን የግብጽፅ ፍላጎት በጉልበት ሌሎች ላይ ሊጫን አይችልም።

በጦርነትም አይሆንም ብለዋል።

‹‹ኢትዮጵያውያን ለግብፅ የተሳሳተ ፍላጎት ሲባል ጥቅማቸውን ዘንግተው እጃቸውን አጣጥፈው መብታቸውን ጥለው ይቀመጣሉ ተብለው አይታሰብም›› ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም ግብፅ በጦርነት ፍላጎቷን ለመጫን ስንት ጦርነት ትዋጋለች? ስንት ጊዜስ ትዘምታለች? የግብፅን ጦርነት በትህትና የሚያስተናግድ ማንን ታገኛለች›› ሲሉም አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የናይል ውሃ አመንጪ አገሮች የራሳቸውን ጥቅምና መብት ጥለው ግብፅን በትህትና አያስተናግዱም።

የጦርነት ሐሳብ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የቂል አስተሳሰብም ጭምር ነው ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፤ በተለይ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ በጦርነት የውሃ ፍላጎቷን ለማሟላት ማሰቧ በዲፕሎማሲና በመተሳሰብ የመሽራት ሐሳቡም ሆነ እውቀቱ ርቋታል ሲሉ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም