የከተማ አስተዳደሩ ለ2013 የትምህርት ዘመን ለ600 ሺህ ተማሪዎች የደንብ ልብስ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

132

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2012 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2013 የትምህርት ዘመን በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ 600 ሺህ ተማሪዎች የደንብ ልብስ እንደሚያቀርብ አስታወቀ።

አስተዳደሩ ከ380 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎችም የምገባ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።

የመማሪያ ቁሳቁስም የሚሟላ መሆኑ ተገልጿል።

የተማሪዎቹን የደንብ ልብስ የማዘጋጀት ሂደት ላይ ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የስነ-ልቦና ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በዛሬው ዕለት የተማሪዎች የደንብ ልብስ ዝግጅት ማስተዋወቂያ ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል።

ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አራት ዓይነት የደንብ ልብስ የተዘጋጀ ሲሆን ለመዋዕለ ህጻናት፣ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል፣ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች የሚሆን ነው።

ለተማሪዎች ምግብ የሚያቀርቡ እናቶችም ልዩ የምግብ ዝግጅት ስልጠና የሚሰጣቸው መሆኑም ተጠቁሟል።

በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ የማብሰያና የመመገቢያ አዳራሾች እንደሚዘጋጁም ተነግሯል።

ወጥ የሆነ የተማሪዎች የደንብ ልብስ በመንግስት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የቀረበው በ2012 የትምህርት ዘመን ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ 400 ሺህ ያህል የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መቅረቡ ይታወሳል።

በተመሳሳይም ከ2012 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በአዲስ አበባ በሚገኙ 223 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተግባራዊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም