ቀጥታ፡

ስፔን የቱሪዝም ዘርፉን ለመጠበቅ 4.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት ይፋ አደረገች

ሰኔ 11/2012(ኢዜአ) ስፔን ኮሮና ኮቪዲ 19 በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከጋረጠበት አደጋ ለመታደግ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር  መመደቧን ይፋ አድርጋለች፡፡

የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግሥት የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ኮሮና ካደረሰብት ኪሳራ እንዲያገግም 4.26 ቢሊዮን ዩሮ ወይንም 4.7 በሊዮን ዶላር መመደቡን አናዶሉ አስነብቧል፡፡

አብዛኛው የገንዘቡ ድጋፍም በአነስተኛ የወለድ ክፍያ ለቱሪዝም ዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚከፋፈል ነው ተብሏል፡፡

አየር መንገዶችም በስፔን አየር ማረፊያ ሲጠቀሙ ከፍተኛ ቅናሽ ይደረግላቸዋል ነው የተባለው፡፡

1.2 ሚሊዮን ሰራተኞችን አቅፎ በያዘው የስፔን የቱሪዝም ዘርፍ ሰራተኞች ሳይባረሩ የሚሰሩበትን ሁኔታ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ አንደሚያከናውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡

ይህም አገርን ማዳን ነው ሲሉ ገልጸውታል ፡፡

እ.ኤ.አ በ2019 ስፔን 83.7 ሚሊዮን ጎበኚዎች ያስተናገደች ሲሆን በዚሁ ዓመት የቱሪዝም ዘርፉ 12 በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷን ገቢ ሸፍኗል፡፡

በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱ አለማቀፍ ማኅበራት እንዳስታወቁት የቱሪዝም ዘርፉ በዚህ ዓመት 93 በሊዮን ዶላር ኪሳራ ሊገጥመው ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም