ቀጥታ፡

የኮሮና መከላከያ ስራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በገበያ እና ግብአት እጥረት ገጠማቸው

ሐዋሳ፣ ሰኔ 11/2012 (ኢዜአ) በገበያ እና ግብአት እጥረት መቸገራቸውን በደቡብ ክልል ለኮሮና ቫይረስ መከላከያነት የሚውሉ የፈጠራ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ገለጹ።

የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በሀዋሳ ከተማ  የሚገኘው የቢ. ኤንድ ኢ ማኑፋክቸርንግ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት በለጠ ስንታየሁ እንዳለው  ከአምስት የዩኒቨርሲቲ  ምሩቃን ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች  ከተሰማሩ ስድስት ወራት ሆኗቸዋል።

በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ለቫይረሱ መከላከያነት የሚውሉ ከእጅ ንኪክ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ እያመረቱ እንደሚገኙ ጠቅሷል።

በተለይ የህይወት መስዋዕት እየከፈሉ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሐኪሞች የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው  ጋር ያላቸውን ንኪክ ለመቀነስ የሚረዳና በ"ሪሞት ኮንትሮል " ታካሚውን ለማንቀሳቀስ የሚችል ዘመናዊ የታካሚዎች አልጋ ማምረታቸውንም አስታውቋል።

የአዲስ ፈጠራ ውጤት የሆነው አልጋ  በዘላቂነት ጥቅም እንዲሰጥ የታሰበ መሆኑን ያመለከተው ወጣቱ  መለዋወጫዎች ያሉትና በዋጋ ደረጃ ከውጭ  ከሚገባው  ቅናሽ  እንዳለውም ጠቋሟል።

ሆኖም  ለምርቶቻቸው  ገበያ   በማጣት መቸገራቸውን ተናግሯል።

በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ቡኢ ከተማ 11 ሆነው በመደራጅት በልብስ ስፌት ስራ መሰማራታቸውን የተናገረው ደግሞ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት አስናቀ አቢያ ነው።

ወጣቱ ለኢዜአ እንደገለጸው የኮሮና መከሰትን ተከትሎ በሥራቸው ላይ መቀዛቀዝ ከመፍጠሩ በፊት ውጤታማ  ነበሩ።

ችግሩን ለመቋቋም ለቫይረሱ መከላከያነት  የሚያገለግሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የጤና ባለሙያዎች ቱታ ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የምርታቸው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም ከግብአት እጥረት የተነሳ በአሁኑ ወቅት ማምረት ማቆማቸውን ጠቅሶ መንግስት ግብዓት የሚያገኙበትን  ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መፈለጋቸውን ገልጿል።

በሀዋሳ ከተማ  የፍሬንድሽፕ ኤሌክትሮመካኒካል ኢንጂነርንግ ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ አስራት አንጁሎ በበኩላቸው ስምንት ሆነው በመደራጀት በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ሙሉ የሰውነት አካልን  በሳኒታይዘር የሚያጸዳ /ቦዲ ሳኒታይዘር/  እጅን በእንፋሎት የሚያስታጠብ  የፈጠራ ውጤቶችን  እየሰራን ነው ብለዋል።

ንኪክን የሚያስቀር የሙቀት ናሙና መቀበያ፣ "ዲጂታል ቬንቲሌሽን" እና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ የሆስፒታል አልጋዎችንም  ማምረት መጀመራቸውንም ጠቅሷል።

ለምርቶቻቸው  የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ  የፈጠራ ስራ ተነሳሽነታቸውን እየተጎዳ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ኢዘዲን ሙስባ በሰጡት ምላሽ  በኮሮና ምክንያት ዘርፉ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመነጋገር የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸውና ዘርፋቸውን ለውጠው  የቫይረሱ  መከላከያ ግብአት ማምረት ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸርንግ ዘርፍ የተሰማሩ ከ262 በላይ ኢንተርፕራይዞች ለኮሮና ቅድመ መከላከል የሚረዱ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችና ግብአቶች እያመረቱ ይገኛሉ ብለዋል።

በፈጠራ የተመረቱ ቴክኖሎጂዎችም ሆነ የፈጠራ ባለሙያዎች ከገበያ ትስስርና ከግብአት እጥረት አንጻር እየተነሳ ያለው ቅሬታ አግባብ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እስካሁንም ከ150 ሺህ ሊትር በላይ አልኮል ከስኳር ኮርፖሬሽን በማስመጣት ለሳኒታይዘር አምራች ማህበራት የተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአንድ ሺህ በላይ አልጋዎችን የክልሉ ጤና ቢሮ ለመረከብ ፍላጎት በማሳየቱ  በሂደት ላይ እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደ አቶ ኢዘዲን ገለጻ ቴክኖሎጂዎቹ ከአጭር ጊዜ መፍትሄነት ባሻገር በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግና ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ድጋፍና ዕውቅና ለመስጠት የጤና ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም