ድርጅቱ በተቋማት የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል በበጎ ፍቃድ እየተረጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ በተቋማት የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል በበጎ ፍቃድ እየተረጨ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) የራሮ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ዞን ድርጅት የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ተቋማት የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል በበጎ ፍቃድ በመርጨት በኮሮናቫይረስ መከላከል ሥራ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።
ድርጅቱ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ቅጥር ግቢ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት አካሂዷል።
በድርጅቱ የማርኬቲንግ ፕሮዳክሽን ማናጀር ወጣት ፍሬዘውድ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።
በተለይም ከጤና ሚኒስቴር በየጊዜው የሚወጡ የመከላከያ መመሪያዎችን በመጠቀም የቫይረሱን ሥርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ወጣት ፍሬዘውድ፣ ድርጅታቸው ሠራተኞችንና አካባቢን ከቫይረሱ ለመከላከል በተቋማት የኬሚካል ርጭት እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የሰዎች እንቅስቃሴና ንኪኪ በሚበዙባቸው ተቋማት በመገኘት ያለምንም ክፍያ የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ማካሄዳቸውን ነው የገለጹት።
የተረጨው ኬሚካል ለ15 ቀናት የሚቆይና ተህዋስያንን በማምከን የቫይረሱን ሥርጭት መግታት የሚያስችል ነው።
በዚህም ድርጅቱ በአገር ላይ የመጣን ወረርሽኝ በመግታትና አገርን ከችግር በመታደግ በኩል የዜግነት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ነው የተናገረው።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ያለችበት ወቅት በመሆኑ ተከታታይነት ያለው የመከላከልና የጥንቃቄ ሥራዎችን ጎን ለጎን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ወጣቱ መክሯል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም ግንባታውን በኃላፊነትና በእኔነት ስሜት ከግብ ማድረስ የሁሉም ድርሻ መሆኑን አንስቷል።
የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክትም እንዲሁ ለአገር ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁሞ "ይህም ተግባር ጥንቃቄ በታከለበት ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብሏል።
ለዚህም ድርጅታቸው ችግኝ በሚተከልባቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት አካባቢውን በፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል እየረጨ መሆኑን አመልክተው፣ ይህ ሥራ በቀጣይም በስፋት እንደሚቀጥል አመልክቷል።
"ወቅቱ መተባበርና መደጋገፍን ይጠይቃል" ያለው ወጣት ፍሬዘውድ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው እርስ በርስ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝቧል።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ በዚህ በችግር ወቅት በተለየ መልኩ ለአገሩና ለሕዝቡ ያለውን አለኝታነት በተግባር እንዲያሳይና በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ ፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልና የንጽሕና መጠበቂያ ሣሙናዎችን በማምረት ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚያግዙ ግብአቶች እጥረት እንዳይከሰት በስፋት እየሰራ መሆኑም አመልክቷል።