በመዘናጋት የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በመዘናጋት የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
መቀሌ፣ ሰኔ10/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በመዘናጋት ምክንያት የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ በመምጣቱ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ።
በመቀሌ ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ቀደማይ ወያነና ሐወልት ክፍለ ከተሞች ማኅበረሰቡ ኮሮናን ለመከላከል እጁን በውኃና ሣሙና መታጠብ እንዲያዘወትር የማነቃቂያ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል።
የማነቃቂያ ፕሮግራሙን ያስጀመሩት በምክትል ርዕስ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር አብረሃም ተከስተ ናቸው።
በዚህ ወቅት እንደተናገሩት መዘናጋት ባስከተለው ችግር የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ መጥቷል።
ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅርበት የሚዋሰን በመሆኑ ለኮሮና ቫይረስ ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ያለው አማራጭ እያንዳንዱ የማኅበረሰቡ አባል ሳይዘናጋ ርቀቱን ጠብቆ እጁን በውኃና ሣሙና በመታጠብ ሕይወቱን ለመታደግ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ 12 ከተሞች የተዘጋጀው ተመሣሣይ ፕሮግራም ኅብረተሰቡ በየጊዜው እጁን በውኃና ሣሙና መታጠብ እንዲለምድ መሆኑም ተመልክቷል።
''እኛ ውኃ ለማቅረብ እናንተ ደግሞ እጃችሁን በመታጠብ ኮሮና በጋራ እንከላከል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ውኃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር ናቸው።
በእያንዳንዱ ሂደት ላይ በሚፈጠር መዘናጋት በሰው ሕይወት ላይ መፍረድ መሆኑን በመገንዘብ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብን ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በውኃ እጥረት ምክንያት እንዳይቸገር ቢሮው ብልሽት ያጋጠማቸው የውኃ ተቋማትና መስመሮችን በመጠገን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ቄስ ገብረ ገብረማርያም በሰጡት አስተያየት ኮሮንና ለመከላከል በሚሰጡ ትምህርቶች ለውጥ ቢኖርም በአንደንድ ወጣቶች ላይ ክፍተት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።
በወጣቶች ላይ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስተካከል ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመሰማራት ትምህርት እየሰጡ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት መብራት አብደላ ናት።
ሕዝብ በሚበዛባቸው ገበያና መሰል አካባቢዎች የእጅ ማስታጠቢያ የውኃ ታንከር መዘጋጀታቸው ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉት ያለውን ጥረት እንደሚያግዝም አመልክታለች።