ለቀጣዩ ትውልድ ፅዱና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር ዛሬ ችግኝ መትከል ይገባል --- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለቀጣዩ ትውልድ ፅዱና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር ዛሬ ችግኝ መትከል ይገባል --- የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012(ኢዜአ) ለቀጣዩ ትውልድ ፅዱና አረንጓዴ አካባቢን እውን ለማድረግ ዛሬ ላይ ችግኝ መትከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት የሃይማኖት አባቶች በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ኤካ ሚሊኒየም ፓርክ ችግኞችን ተክለዋል።
በእለቱም ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ አባቶች ከ2 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡
ከመርሃ ግብሩ በኋላ አባቶች ባስተላላፉት መልዕክት፤ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴና ጽዱ አካባቢን እውን ለማድረግ ዛሬ ላይ ችግኞችን መትከል ያስፈልጋል።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ጸድቀው የአረንጓዴ ልማቱ ሃብት እንዲሆኑ መንከባከብ ይገባልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ስራአሰኪያጅ መልአከ ህይወት አባ ሃይለ ገብርኤል ነጋሽ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ልማትን የእምነቱ አስተምሮት ይደግፈዋል።
በመጀመሪያው የእምነቱ አስተምሮ የአረንጓዴ ልማት የተጀመረው በስነ-ፍጥረት በመጀመሪያው ፍጥረት ውስጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
በቤተክርስቲያኗ አስተምሮ ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች የአረንጓዴ ልማት ተግባራትን እንዲያከናውኑም ያዛል ብለዋል።
የሁሉም እምነት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች እንዲህ ባለ የሀገር ጉዳይ በአንድ ላይ መስራታቸው ለተከታዮቻቸውም ምሣሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሮዘዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ባስተላለፉት ምልዕክትም በአረንጓዴ ልማት በስፋት በመሳተፍ ለመጪው ትውልድ ልማትን ማሻገር አለብን ብለዋል፡፡
"የሰው ልጅና ተፈጥሮ የማይነጣጠሉ ናቸው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በያለበት ቦታ ሁሉ ችግኝ በመትከል እንዲንከባከብ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሓፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ በበኩላቸው፤ ችግኞችን እንድንተክል መነሻ የሆነን ቅዱስ መጽሐፍ ነው ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ ከዚህ ቀደም ያጠፋውን የተፈጥሮ ሃብት ለመተካትም ዛሬ ችግኞችን መትከል ይኖርበታል ነው ያሉት።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ የሰው ልጅና ተፈጥሮ ልዩ መስተጋብር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
እጽዋት ከሰው ልጆች እስትንፋስ ይወስዳሉ የሰው ልጆችም ከእጽዋት ለመኖር የሚያስፈልገውን ዋነኛ ነገር ኦክስጅንን የሚያገኙ በመሆኑ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጀመሩ የሚታወስ ነው።
በመርሃ ግብሩም በመጪው ክረምት በመላ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራበት ይገኛል።