ከንቲባ ታከለ ዑማ ከስፖርቱ ማኅበረሰብ ጋር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ ታከለ ዑማ ከስፖርቱ ማኅበረሰብ ጋር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) ኢንጂነር ታከለ ዑማ "እኔ ስፖርተኛ ነኝ፤ ዛሬ አረንጓዴ አሻራዬን አስቀምጣለሁ!" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀመሩ።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 የስፖርት ማዘውተሪያ በመገኘት ነው።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ እንዲል ያደረጉ አትሌቶች፣ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ መርሃ ግብሩን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ስፖርት እና አረንጓዴ ቦታ እንደማይነጣጠሉ ተናግረዋል።
ይህን በመገንዘብ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ለማኖር የተገኙ ስፖርተኞችን አመስግነዋል።
በጋራ በመሆን የተተከሉ ችግኞችን ለፍሬ እናበቃለን ሲሉም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያዎች በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን በአረንጓዴ ተክሎችም መዋብ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋይ ናቸው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በከተማዋ በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 34 የስፖርት ፌዴሬሽኖች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ለይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተወካዮች አዲስ አበባን አረንጓዴ ለማድረግ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቀዳሚነት እንደሚሰለፉ ተናግረዋል።
አረንጓዴ አካባቢ ከአትሌቶች የሥልጠና ቦታ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በዛሬው ዕለት አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አትሌት ገንዘቤ ዲባባና አትሌት ጌጤ ዋሚ ናቸው።
ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተገቢ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም አትሌቶቹ ተናግረዋል።
የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጥሪ በመቀበል አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።