ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር በዜግነት ዲፕሎማሲ መታገዝ አለበት

ባህር ዳር፤ ሰኔ 10/2012(ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደውን ድርድር በበላይነት ለመወጣት የዜግነት ዲፕሎማሲን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ምሁራን ስታወቁ።

በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም በመጻፍና በመናገር ለዓለም ህዝብ በማሳወቅ የዜግነት ዲፕሎማሲውን ማቀላጠፍ ይገባል ብለዋል።

በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ ለኢዜአ እንዳሉት የአባይ ወንዝን ግብጽ ለዘመናት በብቸኝነት ተጠቅማበታለች።
አሁን ላይ መንግስትና ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልማትን ከማፋጠን ባሻገር ለዘመናት የምትገለጽበትን የድህነትና ኋላ ቀርነት ገጽታ ለመቀየር እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

"የግድቡ ግንባታ ውሃ መያዝ ከሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በተለይም ግብጽ ያረጀውን የቅኝ ግዛት ውል በኢትዮጵ ላይ በመጫን መገለጫችን የሆነውን ፕሮጀክታችን ለማስተጓጎል ጥረት ማድረጓ አግባብነት የለውም" ብለዋል ።

በዚህ ፈታኝ ወቅት "አትዮጵያ የዲፕሎማሲ የበላይነትን በመያዝ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቁሳዊ ሃይልን ማደራጀት፣ የመደራደር አቅምን መገንባትና አዳዲስ የመደራደሪያ ሃሳብን ማመንጨት ወሳኝ ነው" ሲሉም ምሁሩ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜጎች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በሚካሄደው ድርድር የኢትዮጵያን ተደራዳሪዎች ዓላማ በመደገፍ በሚቻለው ሁሉ በመናገር፣ በመጻፍና በመገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ እንደሚገባም ገልፀዋል ።

በዚህም "በዓለም አቀፍ ህግ የተቀመጠውን ውሃውን በምክንያታዊነትና በፍትሃዊነት የመጠቀምና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህን ተከትለን የምናካሔደው ድርድር መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ተግባር መሆን አለበት" ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ አቶ ዘውዱ መንገሻ አንዳሉት ደግሞ ኢትየጵያ በመጪው ክረምት ውኃ ለመሙላት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች።

"ወደ ውሃ ሙሌቱ እየተቃረብን ስንመጣ በመጀመሪያ የግድቡ ግንባታ እንዳይካሄድ ቀጥሎ ደግሞ የግድቡ ርዝመት እንዲቀንስ ስትጥር የነበረችው ግብጽ አሁን ላይ የውሃ ሙሌቱን ለማስተጓጎል እየሰራች ትገኛለች" ነው ያሉት ።

የግብጽ ፍላጎት በህዳሴው ግድብ ላይ ተመስርታ በቀጣይ ኢትዮጵያ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን በአባይ ወንዝ ላይ እንዳትገነባ በሚካሄደው ስምምነት ማሰር ላይ የተመሰረተ የራሷን ኋላ ቀር ፍላጎት ለመጫን ያለመ መሆኑን ገልፀዋል ።

"የኢትዮጵያ ምሁራንም በተፋሰሱ አገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍንና ግብጽ በላይኛው ተፋሰስ አገራት ላይ እያሳደረች ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለዓለም በማሳወቅ መስራት አለብን ብዬ አምናለሁ" ሲሉም ነው አቶ ዘውዱ የተናገሩት።

በተለይም ለዓመታት የተለፋበት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ግብጽ ልዩ ልዩ ሃሳቦችን በማምጣት ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገች ያለውን ተጽእኖ የፍትሃዊነትና የምክንያታዊነትን መርህ በማቅረብ መሞጎት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል ።

ለዚህም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያረጋግጡ ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ስራዎች በማካሄድ አዳዲስና ተገዳዳሪ ሃሳቦችን ወደ ፊት በማምጣት የፍትሃዊነትና የምክንያታዊነት አጠቃቀም መርህን ለማስፈን በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል ።

መንግስትም በአገር ውስጥ የሚስተዋሉ የፖለቲካ ቅራኔዎች በመፍታት፣ ከአጎራባች አገራት ጋር ያለውን ቀጠናዊ ትስስር በማጠናከርና እንደ አፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ያሉ ከባቢያዊ ድርጅቶችን መጠቀም አለበት የሚል ሓሳብ እንዳላቸውም
ገልፀዋል ።

ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋም የህዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት በተጨማሪ ለቱሪዝም፣ ለአሳ ሃብት ልማትና እንችላለን የሚልለውን ስነ ልቦና ለመገንባት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ አንድነቱን አጠናክሮ ድጋፍ እንዲያደርግ ምሁራኑ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም