ኢትዮጵያና ኮሪያ በዘላቂ የደን ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኮሪያ በዘላቂ የደን ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012( ኢዜአ) ኢትዮጵያና ኮሪያ በዘላቂ የደን ልማት፣ እና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለመሸፈን በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል።
የኮሪያ የደን አገልግሎት ሚኒስትር በኢትዮጵያ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በደን ለመሸፈንና በተደጋጋሚ ለግጭት የሚዳረጉ ጎሳዎችን ቀጣይነት ባለው የደን ውጤቶች ተጠቃሚ በማድረግ ትብብራቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራ ኮሪያ ሄራልድ ዘግቧል።
ትናንት በሲኦል ከተማ "ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማላበስ" በሚል ርዕስ በኮሪያ የደን አገልግሎትና በኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና የአየር ጸባይ ለውጥ ኮሚሽን የተዘጋጀው መጽሐፍ ሲመረቅ ፕሮጀክቱ ይፋ ተደርጓል።
በዝግጅቱ ወቅት የጋራ የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመ ሲሆን አጋርነቱ እኤአ በ2030 በኢትዮጵያ አረንጓዴ እድገት እና አለም አቀፍ ግቦችን ለማሳካት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በስራው ላይ ዴንማርክንና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ 12 አጋር ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፍ ፎረሞችን በማዘጋጀትና የመንግስትና የግሉን ዘርፍ በማስተባበር የአየር ፀባይ ለውጥን መቋቋምና፣ ቀጣይነት ያለው እድገትን ማረጋገጥ ላይ እንዲሚሰራ ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ፣ በደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአየር ጸባይ ለውጥ አምባሳደር ዮ ዮን ቹል፣ የግሎባል ግሪን ግሮዝ ዳይሬክተር ጄኔራል ኪም ሃዮ ኡን እና ከብሄራዊ የደን ሳይንስ ኢንስቲቱት ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ተቋሙ እኤአ ከመስከረም 2019 አንስቶ በኢትዮጵያ የደኖች መልሶ ማገገም ፕሮጀክት እቅድና አተገባባር ላይ ሲሰራ መቆየቱ ተጠቅሷል።
በተያዘው ዓመት መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ፕሮጀክቱ "የመነሻ ትብብር" የዓመቱ ፕሮጀክት ሆኖ መመረጡ ተገልጿል።
የኮሪያ የደን አገልግሎት ሚኒስትር ፓርክ ቾንግ ሆፍ በጥር 2012 የደን ልማትን መልሶ ማቋቋም የትብብር ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር አዲስ አበባ ላይ መነጋጋራቸውን ዘገባው አስታውሷል።
ፕሮጀክቱ የሰላም የደን ኢኒሸቲቭ ተብሎ በሙከራ ደረጃ የሚከናወን ሲሆን አገር በቀል ኢኮኖሚን ለማነቃቃት የራሱ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል።
በተጨማሪ የተራቆቱ ደኖች መልሰው እንዲያገግሙና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተስማሚ የሆነ የቡና ልማት በማከናወን አካባቢያዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።
በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነው የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና በግዙፍ የእርሻ ልማት ሳይሆን የተለያዩ ደኖችን በያዘ ጫካ ውስጥ በግዙፍ ዛፎች ተጠልለው ይበቅላሉ ይላል ዘገባው።
ይህ አሰራር ቡናው የራሱ የሆነ የተለየ ጣዕምና ለዛ እንዲኖረው እንደሚያስችለው ተጠቅሷል።
“በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እውን ያደረግነው የሰላም የደን ኢኒሸቲቭ ብዙ ትርጉም የያዘ ነው" ብለዋል ፓርክ።
ፕሮጀክቱ በአገሪቱ የሚገኙት የተለያዩ ጎሳዎች እርስ በአርሳቸው መተማመን እንዲኖራቸው ያስችላል በማለት የኮሪያ የደን አገልግሎት ሚኒስትር ፓርክ ቾንግ ሆፍ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን በድጋሚ አረንጓዴ ለማልበስ በሚደረገው ጥረት ኮሪያ አሻራዋን እንድታሳርፍ እንደሚያስችላትም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።