የደምበኞች የኦንላይን አገልግሎት በቅርቡ ይጀምራል...ጉምሩክ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የደምበኞች የኦንላይን አገልግሎት በቅርቡ ይጀምራል...ጉምሩክ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና የደንበኞችን ጊዜና ወጪ ለመቆጠብ የጉምሩክ አገልግሎት በኦንላይን ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽ አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለፀው የጉምሩክ አገልግሎትን ለማዘመን ከኮሚሽኑ ጋር እየሰራ የሚገኘው እና ሶፍትዌር በማልማት ስራ የተሰማራ “ዌብፎንቴይን” የተሰኘ ድርጅት ለኮሮና መካከል እንዲያግዝ ያደረገው ድጋፍ ርክክብ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ዌብፎንቴይን 550ሺህ ብር የሚገመት ለኮሮና መከላከል የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ ለጉምሩክ ኮሚሽን አስርክቧል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና የዌብፎይቴን የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ኤልያስ ኪ/ማርያም ርክክብ ያደረጉ ሲሆን ቁሳቁሶቹ 5 የኦክስጂን ማምረቻ (ኦክስጂን ኮንሰንትሬሽን) እና 26 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ናቸው፡፡
ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በድጋፉ ወቅት፤ ለኮሮና መከላከል የተደረገው ድጋፍ ተጋላጭ ለሆኑ ሰራተኞችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት በመስጠት ለታለመው አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ለተደረገው ድጋፍ በገቢዎች ሚኒሰቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን መላው አመራርና ሰራተኛ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የዌብፎንቴይን ተወካይ አቶ ኤልያስ ኪ/ማርያም በበኩላቸው ድርጅቱ በአፍሪካ ለአስር አገራት ለኮሮና መከላከል ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ገልፀዋል፡፡
“ኮሚሽኑ የተደረገው ድጋፍ ለተገቢው አገልግሎት እንደሚያውለው ዕምነት አለን” ማለታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።