በህዳሴ ግድብ ላይ ያሉት አለመግባባቶችን ለመፍታት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን ለመጠቀም ከተደረሱ ስምምነቶች ልምድ ሊቀመር ይገባል... ፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማሪያም - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ላይ ያሉት አለመግባባቶችን ለመፍታት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን ለመጠቀም ከተደረሱ ስምምነቶች ልምድ ሊቀመር ይገባል... ፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማሪያም
ሰኔ 10/2012(ኢዜአ) ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ለሚደረረው ጥረት በአሜሪካና ሜክሲኮ መሰል ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን ለመጠቀም ከተደረሱ ስምምነቶች ልምድ ሊቀመር ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማሪያም ተናገሩ።
ፕሮፌሰሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በሚያደርጉት ድርድር ውስጥ የአሜሪካ ሚና በተመለከተ በግላቸው ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ደብዳቤ ጽፈዋል።
በአሜሪካ አደራዳሪነት በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረውን የሶስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ፕሮፌሰሩ በጻፉት ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ከግብጽ ጋር ሲታደርግ በነበረው ድርድር ሰላማዊና የሁለትዮሽን ግንኙነት በጠበቀ መልኩ ቢሆንም ግብጽ ግን በኢትዮጵያ ላይ የአባይን ውሃ በብቸኝነት ለመቆጣጠርና ኢትዮጵያ ሀሳቧን ካልተቀበለች ጦርነት ለመክፈት እየዛተች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ሆኖም የህዳሴ ግድብ ድርድር በአለም አቀፉ የድምበርና የውሃ ኮሚሽን መሰረት መፈታት ያለባቸው በአገራቱ ስምምነት እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።
ለአብነትም ከአሜሪካ የሚነሳው የኮሎራዶ ወንዝ ሜክሲኮ ለመድረስ 7 የአሜሪካን ስቴቶች ያቋርጣል። ከወንዙ 97 በመቶ የውሃ ድርሻ ያላት አሜሪካ በ1944 በተደረሱት ስምምነት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን አክሪ ፊት ወይም 10 በመቶ የውሃውን መጠን ለሜክሲኮ በአመት ትለቃለች።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን መኑሸን በዋሽንግተን ሲደረግ ነበረው የሶስቱ ሀገራት ድርድር ላይ አሜሪካን ወክለው ሲሳተፉ እንደነበር የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፤ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ በድርድሩ መሳተፍ የእሳቸው ሳይሆን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራ ኃላፊነት ነበር ብለዋል በደብዳቤያቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሓዊነትና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወንዙን የመጠቀም መብት እንዳላት አሜሪካ ልትገነዘብ ይገባታልም ነው ያሉት፡፡
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በሶስቱ ሀገራት ስምምነት ተደርሶ በፈረንጆቹ የካቲት ወር 2020 ላይ ሊፈረም የነበረውን ሰነድ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀው፤ በአሜሪካ ድጋፍ ሊቀጥል ከሚችል የትኛውም በግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር ከመጀመሩ በፊት በፈረንጆቹ የካቲት 28 ቀን 2020 ላይ ለፊርማ ቀርቦ የነበረው የስምምነት ሰነድ በይፋ መሻር ይገበዋልም ብለዋል።
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማሪያም በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት ሊቀመንበርም ናቸው።