ቀጥታ፡

ግብጽ መንታ መንገድ በመያዝ የተለመደ አካሄዷን ቀጥላበታለች - ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2012 ( ኢዜአ) የሶስትዮሽ ድርድር ውስጥ የምትገኘው ግብጽ መንታ መንገድ በመያዝ ከድርድር ውጭ ያልተገባ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለፁ።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

ባለፉት አምስት ቀናት የነበረውን የድርድር ሂደት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በየካቲት ወር ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል የሱዳን መንግስት ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

መቼም ቢሆን ችግሮችን በድርድር የመፍታት አቋም ያላት ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚችል ድርድር የማካሄድ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ወደ ድርድሩ የገባችው ግብጽ በአንድ በኩል በውይይት መድረኩ እየተሳተፈች በሌላ በኩል የድርድር ሂደቱን ሊያደናቅፍ የሚችል ድርጊት እየፈጸመች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

''በአንድ በኩል ይደራደራሉ፤ በሌላ መልኩ ወደተለያዩ ዓለም ዓቀፍ አካላት ጉዳዩን ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ'' ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ''ሁለት መንታ መንገድ ይዘው ነው እየተደራደሩ ያሉት'' ብለዋል።

ለግድቡ ስራ ምንም የምትሰጠው የሌላት ግብጽ የሚሰጣትንም ለመቀበል ዝግጁነት እንደሌላት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት በማመን የድርድሩ ሂደት የተሳካ እንዲሆን እየሰራች እንደሆነም ገልጸዋል።

ግድቡ እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት መሆኑን አስታውሰው፤ የዓባይ ውሃ 86 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ሁሉን በመቻል ምንም አስተዋጽኦ ከማታደርገው ግብጽ ጋር ድርድር እያካሄደች መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ይህን የምታደርገው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጽኑ አቋም ስላላት መሆኑንም ገልጸዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የመነቃቃትና የአንድነት ምንጭ መሆኑን ገልጸው፤ በመርህ ላይ ተመስርተን ለድርድር ዝግጁ ሆነን እያለ ግብጾች የተለያየ ምክንያት ፈልገው ድርድሩን ለማቋረጥ ነው ሃሳባቸው'' ብለዋል።

ግብጽ ኢትዮጵያ እንዳታድግ በተለያየ መንገድ ጥረት እያደረገች ብትሆንም ሁሉንም በመቻል ኢትዮጵያ በድርድር ልዩነቱን ለመፍታት እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በእርግጥ ግብጾች የቸገራቸው ውሃ ከሆነ ግድቡ ፋይዳ የሚኖረው ውሃ በብዛት ሲያፈስ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ገዱ፤ ግብጽ የምታማርረው የውሃ ይቀርብኛል ሃሳብ መሰረት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ዕድገት ከማይፈልጉት ግብጾች ጋር በድርድር ሂደት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች አለመኖራቸውን አስታውሰው፤ አሁንም ፍላጎታቸው የ1959 የስምምነት ሰነድ ስራ ላይ እንዲውል መሆኑን አውስተዋል።

ሰነዱ ደግሞ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንን የማይመጥንና የሁሉንም ጥቅም የማያስከብር መሆኑን አክለዋል።

መፍትሄው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን ኢትዮጵያ አምና ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆኗንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ የውሃውን ድርሻ ይዛ በድርድር ውጤት ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ ግብጽ በተቃራኒው በአንድ በኩል የድርድር ሂደቱ ውስጥ እየተሳተፈች በሌላ በኩል ዓለምዓቀፉን ማኅበረሰብ በመጠየቅ በመንታ መንገድ ላይ እየሄደች መሆኗንም ጠቁመዋል።

በዚሁ መሰረት ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ እውነታውን በመረዳት ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አስተላልፈዋል።

ግብጽ የኢትዮጵያን እድገት ለማደናቀፍ የተለያየ ጥረት እንደምታደርግ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ በአንድነት መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም