ባለሥልጣኑ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለሚያመርቱ ድርጅቶች ፈቃድ እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባለሥልጣኑ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለሚያመርቱ ድርጅቶች ፈቃድ እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2012 ( ኢዜአ) የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል /ማስክ/ ለሚያመርቱ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የተለያዩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በባለሙያዎች ተደግፈው እንዲሸጡ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።
በዚህም ከመድኃኒት ቤቶችና ከሱፐርማርኬቶች በተጨማሪ ለዚሁ አገልግሎት ለሚውሉ ሱቆች ፈቃድ መስጠት ጀምረናል ብለዋል።
ሱቆቹ ኀብረተሰቡ በባለሙያ ምክር የተለያዩ አማራጮችን አይቶ እንዲገዛ ያስችላሉ ነው ያሉት።
ለጨርቅ ማስክ አምራቾች ፈቃድ መስጠት መጀመሩንና በእስካሁን ሂደት አንድ አምራች የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲን መስፈርት አሟልቶ ፈቃድ መውሰዱን ተናግረዋል።
የሌሎች አምራቾች ማስኮችም የመተንፈስና ውሃ የመቋቋም አቅም እንዲሁም አፍና አፍንጫን ምን ያህል ይሸፍናሉ የሚለው ናሙና ተወስዶ እየተፈተሸ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም በጎዳናዎች ላይ ማስክ የሚሸጡ ግለሰቦችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እርምጃ መውሰድ ይጀመራል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ በከተማ ደረጃ ከ50 ሺህ በላይ በሚሆኑ ተቋማት ላይ ቁጥጥር በማድረግ የጥራትና የዋጋ ችግር የተስተዋለባቸውን ከማስጠንቀቅ እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል።
ከ53 በላይ መድሃኒት ቤቶች መታሸጋቸውን፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ ከ90 በላይ ለሚሆኑ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ለ42 የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘር አምራቾችና 10 ለሚደርሱ የኬሚካል ርጭት ለሚያከናውኑ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱንም አክለዋል።
ወረርሽኙን የመከላከል ኃላፊነት የሁሉም በመሆኑ ኀብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን ምርቶች ጥራት እንዲያረጋግጥም አሳስበዋል።
የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸውን ምርቶች እንዲጠቀምና መረጃዎችን በባለሥልጣኑ ማኅበራዊ ሚዲያና ድረ-ገፅ ላይ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ከምርት ጥራት ጋር የተያያዘ ማንኛውም አይነት ጥቆማ ለመስጠት የባለሥልጣኑን ነፃ የስልክ መስመር 8864 መጠቀም እንደሚቻልም አስታውቀዋል።