አክሱም ዩኒቨርሲቲ በ3 የትምህርት ዓይነቶች የዶክትሬት ዲግሪ መረሃ ግብር ሊጀምር ነው

261

አክሱም፣ ሰኔ 09/2012 (ኢዜአ) አክሱም ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በሦስት የትምህርት ዓይነቶች የዶክትሬት ዲግሪ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ገብረመድህን መዝገበ ለኢዜአ እንደገለጹት የሚጀመረው  መርሃ ግብር  በአፈር ለምነትና ስነ እጽዋት ንጥረ ነገር ፣በአፈርና ውሃ ጠበቃ ምህንድስና እና በሂሳብ  የትምህርት ዓይነቶች ነው።

መረሃ ግብሩን   ለማስጀምር  ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል  የስርዓተ ትምህርት  ቀረጻና በዚህ ላይ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መካሄዱን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሶስቱ የትምህርት ዓይነቶች  በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ለመማር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር  የሚመድባቸው 37 ተማሪዎችን ለመቀበልና  ትምህርት የሚሰጡ ተባባሪ ፕሮፌሰሮችም መሰናዳታቸውን  አስታውቀዋል።

የዶክትሬት ተማሪዎች   ቁጥራቸው አነስተኛ  በመሆኑ የኮሮና ቫይረስ መቆጣጠር ካልተቻለ  የመማር ማስተማሩ ስራ በ"ኦን ላይ"  እንደሚካሄድ ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ዘርፍ ምሁር ዶክተር ገብረእየሱስ ብርሃ በበኩላቸው የሀገሪቱ  ኢኮኖሚ ዋና ምሰሶ ግብርና መሆኑን ጠቅሰው  ዘርፉን ለማዘመን በጥናት እና ምርምር እንዲደገፍ ለማስቻል ተቋሙ የሚጀምረው መረሃ ግብር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲ በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ምህንድስና የሶስተኛ ዲግሪ መክፈቱ ሀረማያ  ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሁለተኛ  እንደሚያደርገው ያመላከቱት ምሁሩ ፣"በተለይ በአፈር ለምነት እና ስነ እጽዋት ንጥረ ነገር በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ የመጀመሪያ ዩኒቨርሲቲ ያደርገዋል "ብለዋል።

በኢትዮጰያ የሰሜኑ ክፍል  አርሶ አደሮች በግብርናው ዘርፍ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በጥናት እና ምርምር ተደግፉ መለየትና መፍትሄ ማምጣት ብሎም የዘርፉን ልማት ለማሳደግ  የላቀ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በተለይ ለአፈር ለምነት  የትኛው ማዳበሪያ ለየትኛው የአፈር ዓይነት እንደሚሆን በመለየት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚያስችል ጉዳዮችን ትኩረት አደርጎ ለመስራት ያስችላል ብለዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የስነ አዝርእት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኃይለሚካኤል በርሀ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ለመጀመር ያዘጋጀው የትምህርት መረሃ ግብር  መንግስትና ህዝብ በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና  አፈር ለምነት  ለመጠበቅ ለሚከናወኑት ስራ የሚበጅ መሆኑን ተናግረዋል።

''በግብርናው ዘርፍ በተለይ በአፈር ለምነትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘርፍ ላይ በርካታ ምሁራን ያስፈልጋሉ'' ያሉት አቶ ኃይለሚካኤል ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር አርሶ አደሩ እንዲደርሰው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም  ገልጸዋል።

እስከ አርሶ አደሩ ማሳ ላይ በመድረስ የተጀመረው የአፈር ዓይነት የመለየት ስራ ለማጠናከር ያግዘናልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም