ለህዳሴ ግድብ ውኃ በሚያርፍበት ቦታ የደን ምንጣሮ ለማካሔድ የፊታችን ሐሙስ የቦታ ርክክብ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ውኃ በሚያርፍበት ቦታ የደን ምንጣሮ ለማካሔድ የፊታችን ሐሙስ የቦታ ርክክብ ይፈጸማል
አሶሳ ፣ ሰኔ 09 / 2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውኃ በሚያርፍበት ቦታ ላይ የሚገኘውን የደን ምንጣሮ ስራ ለመጀመር የፊታችን ሐሙስ የቦታ ርክክብ እንደሚካሔድ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ ።
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን ሃይል ማመንጨት የሚያስችለው ውሃ የሚተኛበት ቦታ ለማመቻቸት የደን ምንጣሮ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
ምንጣሮውን ከሚያካሂዱ 45 ኢንተርፕራይዞች ጋር ውል መገባቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል ።
የምንጣሮ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሌሎች 25 ኢንተርፕራይዞች በተጠባባቂነት መመዝገባቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ውሃው የሚተኛበት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ለምንጣሮ የተዘጋጀ ሲሆን የፊታችን ሐሙስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በክልሉ መንግስት መካከል ርክክብ ይካሔዳል ብለዋል ።
ለደን ምንጣሮ ስራው ከሚያስፈልገው 33 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ውስጥ በውሉ መሠረት ስራውን ለሚያከናውኑ ኢንተርፕራይዞች የሚተላለፍ 6 ሚሊዮን ብር የቅድሚያ ክፍያ መለቀቁን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሳምንት የምንጣሮ ስራው በይፋ እንደሚጀመርም አስታው ቀዋል፡፡
ከ1 ሺህ 200 በላይ የክልሉ ስራ አጥ ወጣቶች በምንጣሮ ስራው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው ከሚያገኙት ገንዘብ 30 በመቶ በመቆጠብና ጥሪት በማፍራት ወደ ተሻለ ኢንቨስትመንት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ መመቻቸቱን አቶ በሽር አስረድተዋል፡፡
የደን ምንጣሮ ስራውን የሚያካሂዱት ወጣቶች ስራውን በወቅቱ አጠናቀው ለማስረከብ ከወዲሁ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አስገንዝበዋል፡፡
የግድቡን ምንጣሮ ከሚያካዱ ኢንተርፕራይዞች መካከል የአለማየሁና ዘላለም ምንጣሮ እና ጽዳት ኢንተፕራይዝ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ መልካሙ በሰጡት አስተያየት 26 የማህበሩ አባላት የደን ምንጣሮውን ስራ ለመጀመር በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡
በስራው የምንሳተፈው በዋነኝት የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት በማሰብ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚደረገው ዘመቻ ግድቡን ከመጨረስ አያግደንም የሚሉት ሊቀመንበሩ በሥራችን ወቅት የሚያጋጥሙን ችግሮች ቢኖሩም እንኳን የህይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ሥራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል ።