ቀጥታ፡

በአርባምንጭ አሚባራ እርሻ ልማት ድርጅት በደረሰው የእሳት አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

አርባ ምንጭ፣ ሰኔ 9/2012 (ኢዜአ) በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው አሚባራ እርሻ ልማት ድርጅት ላይ በተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ፖሊስ ገለጸ።

የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል ረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት  በእርሻ ልማቱ ላይ  የእሳት ቃጠሎ የደረሰው ዛሬ ከንጋቱ  11 ሰዓት ገደማ ነው።

በአደጋው ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት 210 ኩንታል የተዳመጠ ጥጥ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጸዋል።

የከተማው ፀጥታ ኃይል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና አየር ማረፊያ ሠራተኞች እንዲሁም ነዋሪዎች ባደረጉት ርብርብ ተጨማሪ ጥፋት ሳያስከትል ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

የቃጠሎው መንስኤ ለጊዜው ባይታወቅም ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም