ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

ደሴ ኢዜአ ሰኔ 6/2012 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የፖለቲካ ልዩነቶች ሳይገድባቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ/ኢህአፓ/ ከፍተኛ አመራርና ደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ አቶ መላከ ካሳ እንዳሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብና ሀገርን ይጠቅማል የሚል የየራሳቸው ፖለቲካዊ አካሄድና አሰራር አላቸው፡፡

ሆኖም  በህዳሴው ግድብ ግንባታ  ዙሪያ የመላው ኢትዮጰያውያን የብርሃን ምንጭ በመሆኑ ከመንግስትና ህዝብ  የተለየ አቋም እንደሌላቸው ተናግረዋል።

"የተለያየ የፖለቲካ አካሄድ ብንከተልም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ልዩነት እንደሌለን ሁሉም ማወቅ አለበት ያሉት" አቶ መላከ ለግድቡ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ፓርቲያቸው የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ግብጽ የግድቡ ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ  የለማስተጓጎል የውስጥ ልዩነት ለመፍጠር ጭምር  የምታደረግው ከንቱ ልፋት  ሊሳካ የማይችል በመሆኑ ከድርጊቷ ልትቆጠብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያን ህዝብ ያለ ልዩነት ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ያደረገ  በመሆኑም እስኪጠናቀቅ ድረስ ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበርም በቅርቡ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፓርቲው  መወሰኑን ጠቁመው  ለአባይ በአንድነት እንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡

መንግስትም ከጎኑ መቆማችን ተረድቶ የጀመረውን ምክንያታዊ አቋም በማጎልበት ዲፕሎማሲውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/  የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓይነቱ ኃይሉ በበኩላቸው  ኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሃብቷ   የመጠቀም መብቷ  በማንም ኃይል ሊገታ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

"ግንባታው የማንንም ጥቅም በማይጎዳ መልኩ በመስራት ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴቶቻችን ያስገድዱናል "ያሉት ኃላፊው በማስፈራራት የግድቡን ግንባታ  ለማጓተት የሚደረገው ሴራ ግን ውሃ እንደማይቋጥር  አስታውቀዋል።

ግብጽ የተሳሳተ መረጃ በአለም እያሰራጨች ለማወዛገብ የምታደርገውን ጥረትም እኛ እውነታውን እያሳየን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በድህነት  እየተቸገረ ያለው የኢትዮጰያን ህዝብ ለመታደግ የተፈጥሮ ሀብት አሟጦ በመጠቀም ወደ እድገት ማማ መውሰድ የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል።

"ከድህነት መውጫ ብቸኛ አማራጫችን የአባይ ግድብ ላይ ቅንጣት ታክልም ልየነት የለንም" ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ግቡን እንዲመታ በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ  የድርሻቸውን እንደሚወጡም  አስታውቀዋል።

"በቀጣዩ ወር የሚጀመረው የውሃ ሙሌትም በጉጉት እየጠበቅን ነው" ያሉት ኃላፊው መንግስት የያዘውን አቋም አጠናክሮ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ የሶስትዮሽ ውይይቶችን በጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም