ቀጥታ፡

6 ዩኒቨርሲቲዎች ከአንድ ሚሊዮን 775 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ስራ ጀመሩ

ሰኔ 9/2012 (ኢዜአ )በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ከአንድ ሚሊዮን 775 ሺህ በላይ ችግኞችን  የመትከል እንቅስቃሴ ጀመሩ።

መረሃ ግብሩ በደብረ ብርሃን  ዩኒቨርሲቲ በተጀመረበት ወቅት የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ  ዶክተር ሙሉ ነጋ  እንዳሉት የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ወደ ሚፈለገው ውጤት ለማድረስ የምሁራን ሚና የጎላ ነው።

በዚህም  የአካባቢ ስነ ምህዳር በማጥናትና ተስማሚ ችግኞችን በማቅረብ የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእውቀት ላይ ተመስርተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉስ  ታደሰ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ለማሳካት ዩንቨርሲቲው ከ70 ሺህ በላይ ችግኞችን በማዘጋጀት ተከላ መጀመሩን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ትናንት የተቋሙ  አመራሮች፣ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞችን በማሳተፍ  ከአንድ ሺህ 600 በላይ ችግኞች መተከላቸውን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ መረሃ ግብሩ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ እንደገለጹት የሚተከሉ ችግኞች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም የሚያግዙ  ናቸው።

ለዚህ ተቋሙ የድርሻውን ለመወጣት  ከ900 ሺህ በላይ ችግኞችን በራሱ አዘጋጅቶ ትናንት የተቋሙ ማህበረሰብ  ቤዛዊት ማርያም  በተባለው ስፍራ  መትከል መጀመሩን ተናግረዋል።

ስራው ለቀጣይ ሁለት ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

በሌላ በኩል የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ሲያስጀምሩ  በችግኝ ተከላው ሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ እንዲሳተፍ  ይደረጋል ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ 13 ዓይነት የሃገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው 250 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

የሚተከሉትን ችግኞች ለማጽደቅ   ክትትልና እንክብካቤ ከማድረግ ባሻገር  በቋሚነት የሚከታተሉ የግብርና ባለሙያዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በጦሳ ተራራና ደሴና ኮምበልቻ ካምፓሶች የሚተከሉት ችግኞች ለአካባቢ ውበትና ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንትና የአስተዳደር ሰራተኞች ለቡና ጥላና ለአፈር ለምነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ዋንዛና  ሌሎች ሀገር በቀል ዛፎችን ያካተተ ችግኝ ትናንት ተክለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶክተር ችሮታው አየለ እንዳሉት ተቋሙ የአካባቢውን የደን ልማት ለማገዝ  የዕጽዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል በማቋቋም ለመጥፋት የተቃረቡ እጽዋቶችን ጥበቃና የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው።

የኮሮና ቫይረስ ከመከላከሉ በተጓዳኝ  የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብርን በመደገፍ  ዩኒቨርሲቲው  የድርሻውን ለመወጣት የችግኝ ተከላ ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የዕጽዋት ጥበቃና ኢ ኮቱሪዝም ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ሟንዳ በበኩላቸው በማዕከሉ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ የተተከሉ ከ50 ሺህ በላይ ችግኞች በመንከባከብ 98 በመቶዎቹ መጽደቃቸውን አመልክተዋል።

ዘንድሮም የትናንቱን ጨምሮ እስካሁን ከ5 ሺህ 500 በላይ ችግኞች መትከላቸውን  ጠቁመዋል።

በችግኝ ተከላ መረሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሃዬሶ   ተቋሙ በቀጣይ ሁለት ወራት ከ30 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን ተናግረዋል።

በሌላ ዜና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ከ150 ሺህ በላይ ችግኞች መጽደቃቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት  ዶክተር ከማል አብዱራሂም ገልጸዋል።

ዶክተር ከማል ይህንን የገለጹት የቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ችግኝ በተከሉበት ወቅት ነው።

ዘንድሮው ቀደም ሲል በተካሄዱ የችግኝ ተከላ ወቅት የታዩ ክፍተቶች በማስተካከል ለሀገራዊው አረንጓዴ አሻራ  መረሃ ግብር አስተዋጽኦ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቢዝንስ እና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ  ክረምት 50 ሺህ ችግኝ እንደሚተከል አመልክተዋል፡፡

የሚተከለው ችግኝ  የጥላ፣ የውበት ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ አምስት መቶ ሺህ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኖች በመትከል የዘንድሮን አረንጓዴ መርሃ ግብር ለማገዝ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን   የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ ገልጸዋል።

የተከላ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ   ሁለት መቶ ሺህ የቡና ፣ ፍራፍሬና የውበት ችግኞች መተከሉን አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ታምራት ታገሰ በበኩላቸው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳካት  የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ  አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም