በውጭ ሃገራት የአበባ ግብይቱ በመሻሻሉ ምርቱን እየላክን ነው... ጣና ፍሎራ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሃገራት የአበባ ግብይቱ በመሻሻሉ ምርቱን እየላክን ነው... ጣና ፍሎራ
ባህር ዳር፣ ሰኔ 9 /2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የውጭ ሃገራት የአበባ ግብይት እየተሻሻለ በመምጣቱ ምርቱን እየላከ መሆኑን በባህር ዳር የሚገኘው የጣና ፍሎራ አበባ ልማት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ማርኬቲንግ የስራ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአበባ ልማት ዘርፉ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ።
በተለይም ቫይረሱ በተከሰተባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት ሃገራቱ የጣሉት የእንቅስቃሴ እገዳ የተመረተው የአበባ ምርት ጭምር ለብልሽት ተዳርጓል።
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ዋና የአበባ ምርት የሽያጭ ወቅት መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን የቫይረሱ መከሰት ገበያውን አቀዝቅዞት ማለፉን ተናግረዋል ።
በተለይም በመጋቢት ወር የአበባ ምርት ሽያጭ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ድርጅቱ 35 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ የአበባ ግብይቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከነበረበት መቀዛቀዝ ወጥቶ መሻሻሉን ጠቅሰው ባለፉት አምስት ወራት 14 ሚሊዮን 180 ሺህ የአበባ ዘንጎችን ወደ መካከለኛውና ምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ተልኳል።
በተለይም በግንቦት ወር 2012 ዓ/ም ብቻ በተደረገው ግብይት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የአበባ ዘንግ ወደ ውጭ ሃገራት መላኩን አስታውቀዋል።
ከተላከው የአበባ ምርትም 2 ሚሊዮን 454 ሺህ ዩሮ እና 135 ሺህ 249 የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።
ለአለም ገበያ ከቀረቡት የአበባ ምርቶች መካከልም አፐርክላስ፣ ፊሮዛ፣ ቡሩንዲ የተባሉና ሌሎች 19 ዓይነት በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የአበባ ምርቶች እንደሚገኙበት ገልፀዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው የግብይት መቀዛቀዝም አሁን እንደገና አንሰራርቶ ቀድሞ ወደ ነበረበት የግብይት ስርአት ተመልሷል ብለዋል።
የቫይረሱ የቆይታ ጊዜ ሊራዘም ይችላል በሚል ትምበያ ድርጅቱ በአበባ እያለማው ካለው 37 ሄክታር መሬት ውስጥ 5 ነጥብ 2 ሄክታሩን ወደ ቀይ ሽንኩርት ልማት ቀይሮ እያለማ መሆኑን ገልፀዋል።
ድርጅቱ በችግሩ ወቅትም በውስጡ የሚሰሩ 800 ሰራተኞችን ይዞ መዝለቁን ያስታወሱት አቶ አብነት ሰራተኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በፈረቃ እንዲገቡና አስፈላጊው የመከላከያ ግብአት በማቅረብ የልማት ስራው እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል ።
ከድርጅቱ ሰራተኞች መካከል ወጣት መልካም ፈንታቢል በሰጠችው አስተያየት ቫይረሱ እንደተከሰተ ገበያ ሲቀዛቀዝ ከስራ እቀነሳለሁ የሚል ስጋት አጋጥሟት እንደነበር አስታውሳለች።
ነገር ግን እስካሁን የተቀነሰ ሰው እንዳላየችና እንዳልሰማች ገልጻ ቫይረሱን ለመከላከል ድርጅቱ ማስክን ጨምሮ እስፈላጊ ግብአቶች እንደሚቀርብላቸው ተናግራለች ።
በቫይረሱ ምክንያት የገበያ መቀዛቀዝ ሲከሰት "እቀነሳለሁ የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር" ያለው ደግሞ ሌላው ሰራተኛ ወጣት ስመኘው መንጌ ነው።
ነገር ግን ድርጅቱ የአበባ ምርት ሽያጩ ቢቀዛቀዝ እንንኳ ሰራተኛውን ለማቆየት በአበባ ምርት ተይዞ የነበረን መሬት ወደ ሽንኩርት የመቀየር አማራጭ መውሰዱ እንዳስደሰተውና እፎይታ እንዲሰማው እንዳደረገው ገልፇል ።
የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብአቶችን በማቅረብ በኩል የተወሰኑ ክፍተቶች ቢኖሩም በአመዛኙ ጥሩ መሆኑን ተናግሯል ።
ጣና ፍሎራ በተያዘው የፈረንጆች በጀት ዓመት 6 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።