“የትግራይ ህዝብ ባለፉት 2 ዓመታት አገር እያዳነ ነው ” ... አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
“የትግራይ ህዝብ ባለፉት 2 ዓመታት አገር እያዳነ ነው ” ... አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል
በህዝቦች ትግል የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የትግራይ ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጥሞናና እርጋታ ውስጥ ሆኖ አገርን እያዳነ ቆይቷል ሲሉ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል ተናገሩ።
አቶ ነብዩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ እንደ አገር የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የትግራይ ህዝብም የራሱን እርምጃ ከወሰደ ወይም በዛ ፍጥነት አገራዊ ለውጡን ደግፎ ከወጣ ከህወሓት ባህሪ አንጻር ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ስላልሆነ ነገሮችን ሰከን ብሎ የማየት ስራሲሰራ ቆይቷል።
በዚህ የትግራይ ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገርን እያዳነ ነው ያሉት አቶ ነብዩ ፣ ከዚህ በተቃራኒው ህወሓት በክልሉ የከፋ አፈናና ጭቆና እያደረሰ፤ ሌላ እድል እንደሌለው በማሰብም "የጣእረ ሞት አይነት እርግጫ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ተግባር እየፈጸመ ይገኛል" ብለዋል።
ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አንጻር ህወሓት ቀላል ኃይል አይደለም ያሉት አቶ ነብዩ፤ በአንድ እርምጃ ጥግ ማስያዝ ስለማይቻል እና ብዙ መዘዝ ሊያመጣ ስለሚችል የትግራይ ህዝብም ጉዳዩን በሰከነ መንገድና በጥሞና እየተመለከተ ቆይቷል ብለዋል።
ይህ ተግባር አገር የማዳን ተግባር መሆኑንና ሁሉም መውሰድ የሚችለውን እርምጃ ወደ መውሰድ ከገባ የለየለት ችግር ሊፈጠር ይችል ነበር ያሉት ሃላፊው ፣ የትግራይ ህዝብ ነገሮችን በጥሞና እያየ ቆይቷል ፤ ይህ ጥሞናውም አገር የማዳኛ ትልቅ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
የትግራይ ህዝብ ለዚህ ተግባሩ ትልቅ ምስጋና የሚቸረው መሆኑን በመጥቀስ ፤ የትግራይ ህዝብ ነገሮችን በጥሞና ይመለከታል ማለት ግን መጥፎና ጥሩውን ለይቶ መሄድ እንዲችል እና ለመወሰንም እንዲመቸው እርምጃውን በስክነት የሚከውን መሆኑን የሚያሳይ እንጂ የትግራይ ህዝብ መጥፎ ነገር ይሸከማል ማለት እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የትግራይ ህዝብ በአጋጣሚው ለህወሓት ተጨማሪ እድል እየሰጠው ነው ያሉት አቶ ነብዩ ፤ ህዝቡ ይሄን ሲያደርግም ከውድቀታቸው ተምረው በተሻለ ሃሳብና አካሄድ በመጓዝ የአገርን ህልውና እና የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚነትም ያስጠብቃሉ የሚል ተስፋ ኖሮት እንደነበርም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያም የክልሉ ህዝብ ለህወሓት የሰጠው አንድ የመጨረሻ እድል እንዳበቃለት አሁን ግልጽ ሆኖ በተለያየ መልኩ በትግራይ ውስጥ የህዝብ እንቢተኝነት፣ የወጣቶች አመጽ እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ ነብዩ እንደሚሉት" ህወሓት በህዝብ የተሰጠውን አንድ እድል መጠቀም አልቻለም፤ይልቁንም አሁንም በባሰ መልኩ አንባገነንነቱንና ኃላፊነት የጎደለው ተግባሩን፣ ብዝበዛውን፣ የመልካም አስተዳደር እጦቱን፣ ሁሉንም ነገር ወደባሰ ደረጃ እየወሰደው ነው። በዚህ ሰዓትም በትግራይ በጣም አሳሳቢ እና ከፍተኛ የሆነ አፈና፣ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ ግድያን ጨምሮ እየተፈጸመ ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ የህወሓትን ፕሮፖጋንዳም ሆነ የለውጡን ጉዞ በአግባቡ መገንዘቡን የጠቆሙት አቶ ነብዩ፤ ህዝብም በከፍተኛ ንቃት ውስጥ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትም ሆነ ብልጽግና ፓርቲም ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ተቃርኖ እንደሌለውና ሊኖረውም እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በፓርላማ ማብራሪያቸው ላይ በግልጽ ማስቀመጣቸውንም ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትፈጠርና አገራዊ አንድነት እውን እንዲሆን ትልቅ ስራ የሰራ እና በሂደቱ ላይም ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ መሆኑንም አቶ ነብዩ አብራርተዋል።
አገራዊ ለውጥም የትግራይ ህዝብም ፍላጎት እና የትግል ውጤት በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ከአገራዊ ለውጡ ወደኋላ የሚሸሽበት ምንም ምክንያት አይኖርም በማለት፤ ይህም የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው የሚለውን ማደናገሪያ ውድቅ ያደረገ ተግባር ነው ብለዋል።
አንድን ህዝብ ፓርቲ ነው ብሎ ከአንድ ድርጅት ጋር እኩል ማየት ስድብ እና ወንጀል ነው ያሉት ሃላፊው፤ ህወሓትም ከዚህ በኋላ የትግራይ ህዝብን የሚክስበትም የሚያገለግልበትም አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለውም ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብ የሰጠው አንድ እድልም በመጠናቀቁና እድል ቢሰጠውም መሻሻልና መለወጥ ባለመቻሉ፤ በፍጥነት በአዲሱ ትውልድ ኃይል መተካት እንዳለበት ግልጽ የሆነበት ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።
ህዝቡም የአዲሱ ትውልድ ፓርቲዎችና ኃይሎች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ትልቅ ፍላጎት እያሳየ መሆኑን ነው አቶ ነብዩ ያመለከቱት።
/ኢፕድ/