ቀጥታ፡

በድርቅ ወቅት የሕዳሴ ግድቡ የስራ ክንውን የሶስቱን ሀገራት የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት ኢትዮጵያ ገለጸች

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2012(ኢዜአ) በድርቅ ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝና አጠቃላይ ስራ የሶስቱን አገራት የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ ሂደት መከተል እንደሚገባ ኢትዮጵያ አስታወቀች።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ አሞላል ሂደትና ዓመታዊ የስራ ክንውን መመሪያዎችና ደንቦች ላይ የጀመሩት የሶስትዮሽ ድርድር ትናንት ለአምስተኛ ቀን ቀጥሎ ውሏል።

በግብጽ ሊቀመንበርነት የተካሄደው የትናንቱ የቪዲዮ ውይይት በሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያ የውሃ አሞላልና ዓመታዊ የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ባተኮሩ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መደራደራቸውን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በድርድሩ ከትናንት በስቲያ በነበረው ውይይት የተነሱ ጉዳዮችን በዕለቱ የድርድሩ ሊቀመንበር የነበረችው ሱዳን ጠቅለል አድርጋ ያቀረበች ሲሆን በሀሳቦቹ ላይ ከመግባባት መደረሱ ተገልጿል።

የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ ውሃ አሞላል ሂደት፣ የዓባይ ወንዝ የተፈጥሮ ፍሰት መጠን፣ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ አሞላል ሂደት መመሪያዎች፣ የድርቅ አስተዳደር ደንቦች፣ የግድቡን ደህንነት የተመለከቱ ደንቦች፣ የአካባቢና የማኀበራዊ ተጽዕኖ ጥናቶች፣ የመመሪያዎቹና ደንቦቹ ወደ ስራ መግባት ሶስቱ አገራት መግባባት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የትናንቱ ድርድር በዋነኛነት ያተኮረው የድርቅ አስተዳደር ደንቦች ተፈጻሚነት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ሂደትና የስራ ክንውን ወቅት ምን መምሰል አለበት? በሚለው ጉዳይ  እንደሆነም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ድርቅ ቢከሰት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የግድቡ ስራ ክንውን ምን መሆን አለበት? በሚለው ጉዳይ የሶስቱን አገራት የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ ሂደት መከተል እንደሚያስፈልግ አስታውቃለች።

ከዚህ ቀደም በነበሩ የሶስትዮሽ ውይይቶች ድርቅ ቢከሰት የሕዳሴ ግድቡ ውሃ አያያዝ ምን መምሰል አለበት? በሚለው ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን በአሃዝ አስደግፈው ያቀረቡትን ሀሳብ ግብጽ እንዳልተቀበለችው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ አሞላል ሂደትና ዓመታዊ የስራ ክንውን መመሪያዎችና ደንቦች ላይ የሚያደርጉት ውይይት ዛሬም የሚቀጥል ይሆናል።

ከውሃ ሚኒስትሮቹ ውይይት ቀደም ብሎም የሶስቱ አገራት የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ዋነኛ ተብለው በተቀመጡ የሕግ ጉዳዮች ላይ የሚወያይ ይሆናል።

የዛሬው የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ድርድር በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት የሚመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም