የኮሮናን ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግሥት ለግብርና ግብአቶች ድጎማ ሊያደርግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናን ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግሥት ለግብርና ግብአቶች ድጎማ ሊያደርግ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትልውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ለግብርና ግብአቶች መንግሥት ድጎማ ሊያደርግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የግብአት አቅርቦቶች ላይ የመንግሥት ድጎማ ያስፈልጋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ደረጀ ደጀኔ እንደሚሉት በግዥ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረትና የኮቪድ- 19ን ወረርሽን ተፅዕኖ ለመቋቋም በግብርና ግብአቶች ላይ የመንግሥት ድጎማ አስፈላጊ ነው።
በአፍሪካ ጋና፣ ማላዊና ሞዛምቢክን የመሳሰሉ አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው በእርሻ ማዳበሪያ አቅርቦታቸው ከ50 እስከ 90 በመቶ ድጋፍ ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያም ይህ ተሞክሮ ተግባራዊ ቢደረግ በግብርና ምርቶች ላይ ውጤታማ ለውጥ ሊያምጣ እንደሚችል ምክራቸውን ሰንዝረዋል።
ይህ ስትራቲጂ የአርሶ አደሩን ጫና ከመቀነስ በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እገዛ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሲቪልቨሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ናዚድ ናስር በበኩላቸው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርሶ አደር እንደመሆኑ ግብርና ላይ ትኩረት መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ 60 በመቶው አርሶ አደሮች ትናንሽ ማሣ ያላቸው በመሆኑ ከዕዳ ጫና ተላቀው ምርታማ እንዲሆኑ የመንግሥት ድጎማ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
በኮቪድ-19 ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ለሚገቡት የአግልግሎት ዘርፉና የኢንዱስትሪ አምራቾችም መደገፍና ለወጣቶች የወለድ ምጣኔን በመቀነስ ብድር መስጠትና ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ችግር ሊገጥም ስለሚችል አርሶ አደሮች ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን በብዛት እንዲያመርቱ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ለጥጥ ምርት ምቹ በመሆኑ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካትም ይቻላል ብለዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዳይጎዳና አርሶ አደሩንም በምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘርፉ በብዙ መልኩ ማሻሻል እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።
በኮቪድ -19 ምክንያት የአገልግሎት ዘርፍንና በሌሎች መስኮች በሚፈጠረው መቀዛቀዝ የሥራ አጥነት ቁጥር እንዳይጨምር ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል ብለዋል።