ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል 359 ሺህ ሄክታር መሬትን በችግኝ ለማልማት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ ሶዶ፣ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል 359 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባላቸው ችግኞች ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ መና ለኢዜአ እንደገለጹት ስራው እየተካሄደ ያለው  በበጋ ወራት የክልሉን ህዝብ በማንቀሳቀስ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በተከናወነባቸው  ስፍራዎች ነው።

በዚህም  3 ሺህ 760 ንዑስ ተፋሰሶች ውስጥ እና 359 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ  አንድ ቢሊዮን 500ሚሊዮን  የደን ፣ የእንስሳት ፣ የደጋ ፣ ወይና ደጋና የቆላ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል  ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ከ220 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለው በየደረጃው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ችግኞቹ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር  የአፈር ለምነትንና ጤንነትን ለማሻሻል፣ የአካባቢ አየር ሚዛን ለመጠበቅ ፣ ጎርፍን ለመቀነስ ብሎም ለእንስሳት መኖ ጭምር የሚያገለግሉ  ናቸው።

እስከ ነሐሴ 2012 ዓ.ም መጨረሻ የሚቀጥለው ይሄው ስራ  አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን  በመጠቀም አርሶና አርብቶ አደሩን በማሳተፍ የሚካሄድ ነው።

የግብርና ባለሙያውና አመራሩም ተመሳሳይ ጥንቃቄ በማድረግ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ  አቶ መለሰ አብራርተዋል።

የወላይታ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዛራ  በበኩላቸው በዞኑ እስካሁን  ከ80 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላው ስራ በተለይ ለደን ልማቱ ስኬት በዞኑ አምስት ወረዳዎች  ከ20 በላይ ደን አልሚ ማህበራትን ተጠቃሚ እያደረገ ከሚገኘው ካርበን  ፕሮጀክት ጋር በቅንጅት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ ደኖችን መልሶ በማልማት የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባሻገር የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ  እንደሆኑ  ጠቅሰዋል።

በሆቢቻ ወረዳ የፕሮጀክቱ  ተጠቃሚ አርሶ አደር ቦጋለ ጮሎ በሰጡት አስተያየት ከሰብል ልማት በተጓዳኝ  ለግንባታ የሚውል የጣውላ ዛፍ በብዛት በማልማትና ለሽያጭ በማቅረብ ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኘውን ደን በመጠበቅና በመንከባከብ  ከካርበን ፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ  በማግኘት ተጠቃሚ እንደሆኑ ጠቁመው  በአካባቢው የተፈጥሮ ደን በመጨመሩ የሰብል ማሳቸው ከጎርፍ ናዳ አደጋ መጠበቁን አስረድተዋል።

መንግስት በሰጣቸው 2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ዓመቱን ሙሉ ችግኝ በማባዛት እየተጠቀሙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በቦሎሶ-ሶሬ ወረዳ  የፍራፍሬ፣ ደን፣ እንስሳት መኖ ችግኝና ዘር አቅራቢ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አማረ አበበ ናቸው።

በዓመት የተዳቀለና  የተሻሻለ  ማንጎና አቮካዶ   ጨምሮ  አንድ  ሚሊዮን 250 ሺህ ያህል  የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በማፍላት ለአልሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያሰራጩ አስረድተዋል።

ይህም ልማቱን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ተጠቃሚ እንደሆኑም  አመልክተዋል።

በተለይ አንድ የአቮካዶ ችግኝ እስከ 500 ፍሬ የማፍራት አቅም ያለው በመሆኑ በአርሶ አደሩና በሌሎችም አልሚዎች ዘንድ እንደሚፈለግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም