የሕግች አለመሻሻልና በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆን ጾታዊ ጥቃት እንዲባባስ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የሕግች አለመሻሻልና በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆን ጾታዊ ጥቃት እንዲባባስ አድርጓል
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) የወጡ ህጎች በየጊዜው አለመሻሻልና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ አለመደረግ በጾታዊ ጥቃት ዙሪያ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲስፋፉ ማድረጉ ተገለጸ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራትና ሴት የሕግ ባለሙያዎች እንዳሉት ኢትዮጵያ በሴቶችና ሕፃናት መብት ዙሪያ ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ጀምሮ ሌሎች ያጸደቀቻቸው ደንቦችና መመሪያዎች አሏት።
ይሁንና በሕጉ ተፈጻሚነትና ተግባራዊነት ላይ ክፍተት ከመኖሩ ባለፈ የሚሰጠውም ፍርድ ተመጣጣኝ አንዳልሆነ ተናግረዋል።
ይህም በተለይ ለችግሩ መስፋፋት መንስኤ ከመሆኑ ባሻገር የጥቃቱ ሰለባ በሚሆኑት ላይም አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው የገለጹት።
ወይዘሮ ሌንሳ ቢዬና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር በቤት ውስጥ ጥቃት ያሉን የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ በድጋሚ መታየት እንዳለበት ገልጸው ኅብረተሰቡን የሚያስተምር ቅጣት የማውጣትና የማስወሰን የአስፈጻሚው አካል ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ወይንሸት ብዛሌ በአዲስ አበባ መንደርን መሰረት ያደረገ አሳታፊ አስተዳደር ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዳይሬክተር በበኩላቸው የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት እየጨመረ የመጣው በዋነኛነት ከአመለካከት ጀምሮ የሕጎቻችን መላላት መሆኑን ገልጸው ይዘቱን እያከበደው የመጣው የሚሰጠው ፍርድ በጣም አነስተኛና የሕግ ማዕቀፉ አስተማሪ አይደለም ብለዋል።
ሁልጊዜ እንዲህ ከበድ ያለ ነገር ሲመጣ መጮህ እንጂ ነገሩን ከሥር ለማስቀረት ሥር መሠረቱ ምንድነው ብለን መንግሥትም ትኩረት አድርጎ ሁላችንም በደንብ ሄደን ያመጣነው ለውጥ የለም ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የምወድሽ በቀለ የሴቶች ይችላሉ ማኅበር ዳይሬክተር ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ማኅበር ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን እንደተናገሩት በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ዜጎችን አካልጉዳተኛ በማድረግ፣ ሕይወት እየቀጠፉ ለሥነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ እየዳረጉ ነው።
ሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች፤ ከሕግ ቅጣት አፈጻጸምና ከቅጣት ስሌት ጋር ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ያለው ሕግ በአግባቡ ፈጽመን ቢሆን ኖሮ ብዙ ችግሮች ሊቀረፉ ይችላሉ ብለው ያስባሉ ወይዘሮ ሳባ"
በመሆኑም በተለይ መንግሥት ለችግሮቹ ትኩረት በመስጠት መመሪያዎችንና ሕጎችን ማስተካከልና የቅጣት ማሻሻያዎችን ማድረግ አለበት በማለት ጠቁመዋል።
የሌላውን ችግር እንደ ራስ ችግር በማየትና ለአጥፊዎችም ተመጣጣኝና በሚያስተምር መልኩ በመቅጣት ለችግሩ እልባት ማበጀት ይገባልም ነው ያሉት።
በማንኛውም የፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ጾታዊ ጥቃትን መሠረት ባደረገ መልኩ እርምጃዎች የሚወሰዱበትን የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ እንዲሚገባም አመልክተዋል።
ባለፉት 9 ወራት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ349 በላይ የሴቶችና ህጻናት ጥቃት ጥቆማዎች የቀረቡ ሲሆን ከ209 የሚበልጡት በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ 89 ሲሆኑ በ12ቱ ላይ ደግሞ ውሳኔ መተላለፉን ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።