ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህጻናት ቀን የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/20-12(ኢዜአ) የአፍሪካ ህጻናት ቀን በኮቪድ-19 ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግና ግንዛቤ በመስጠት እየተከበረ መሆኑን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉን እያከበረ ያለው  ''ህጻናትን ከወረርሽኝና ከጥቃት በመታደግ አረንጓዴ ልማትን ባህል ያደረገ ትውልድ እንፍጠር'' በሚል መሪ ቃል ነው።

በዓሉን ህጻናት፣ ባለድርሻና አጋር አካላት በመሳተፍ በተለያዩ ትምህርት ሰጪ መርሃግብሮች እያከበሩት ይገኛሉ።

በዓሉ ዛሬ በኤስ.ኦ.ኤስ የህጻናት መንደር ሲከበር የተገኙት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ወይዘሮ ፌልሰን አብዱላሂ ቀኑ በህጻናት ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በማውገዝ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የዘንድሮ የአፍሪካ ህጻናት ቀንን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት ጭምር እየተከበረ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባና በክልል ላሉ የሴቶችና ህጻናት መንደር ማዕከላት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 

"ወላጆችና ማህበረሰቡ ለህጻናት መልካም አርአያ በመሆን በቀጣይ ህጻናት አካባቢያቸውን የሚወዱና የሚንከባከቡ እንዲሆኑ ኃላፊነቱን መወጣት አለባቸው" ብለዋል።

በህጻናት ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትም ህጻናት ሊፈጸሙባቸው ከሚችሉ የተለያዩ ጥቃቶችና ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ችግሮች ሊታደጓቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኤስ.ኦ.ኤስ የህጻናት መንደር ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንደተናገሩት የህጻናት መንደሩ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህጻናትን አሳድጎ ለቁም ነገር አብቅቷል።

በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የዘንድሮው የህፃናት ቀን በማዕከሉ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ህጻናት የማህበረሰቡ ውጤት መሆናቸውን አስታውሰው በቀጣይ አገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የማህበረሰቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ የአረንጓዴ አሻራ ቀንን ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት በህጻናት መንደሩ ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል።

በዓሉ በአፍሪካ ለ30ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ ያለው።

የአፍሪካ ህጻናት ቀን እኤአ በ1976 በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ከተማ በግፍ የተጨፈጨፉ ንጹሃን ታዳጊ ህጻናትን ለማስታወስ በየዓመቱ ሰኔ 9 የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም