ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ከድምጻውያን ጋር ችግኞች ተከሉ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ከድምጻውያን ጋር ችግኞች ተከሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከድምጻውያን ጋር በመሆን በየካ ተራራ ችግኞች ተከሉ።
የአረንጓዴ አሻራ የሆነው የችግኝ ተከላ መርሐግብር የተከናወነው በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ ነው።
ኢንጂነር ታከለ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ዓለምአቀፍ ወረርሽኙን ኮቪድ-19 ከመከላከል በተጓዳኝ ነዋሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ችግኞች እንዲተክሉ አሳስበዋል።
ችግኝ ከመትከል ባለፈም ችግኞች በየጊዜው መንከባከብም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ኅብረተሰቡ ችግኞች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት መትከልና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
ኅብረቱም የተከላቸውን ችግኞች ለመንከባከብም ቃል ገብተዋል።
በሥፍራው ተገኝቶ አረንጓዴ አሻራ በማኖሩ ደስተኝነቱን የገለጸውና ተግባሩ መቀጠል አለበት ያለው ድምፃዊ ነዋይ ደበበ ነው።
''ንጹህ አየር ለሰው ልጅ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ችግኝ መትከል ግዴታ ነው። በዚህም ቦታ ተገኝቼ አረንጓዴ አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ'' ሲል የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ተናግሯል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በከተማው አስተዳደር ሰባት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል።
በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከሚተከሉት መካከል ለጥምር ግብርና የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች ይገኙበታል።