ቀጥታ፡

ባለፉት 24 ሰዓት ተጨማሪ 176 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ3 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5636 የላብራቶሪ ምርመራ 176 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ 3 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3ሺህ 521 ደርሷል፡፡

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 175 ሰዎች ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ 1ዱ የውጭ ሀገር ዜጋ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 116 ወንድና 60 ሴት እንዲሁም የዕድሜ ክልላቸው ከ5 ወር ህጻን እስክ 90 አመት እንደሆነ ታውቋል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 98 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ 3 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 2 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 31 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 7 ሰዎች ከሱማሌ ክልል፣ 33 ሰዎች ከአማራ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የ 3 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ሁለቱ በህክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው የቆዩ፣ 1ሰው ደግሞ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆናቸው ታውቋል።

በዚህም አጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 60 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 75 ሰዎች ( 31 ከአዲስ አበባ፣ 28 ሰዎች ከሱማሌ ክልል፡ 10 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 1 ሰው ከአፋር፣ 5 ሰዎች ከአማራ ክልል ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 620 መድረሱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በጽኑ ህክምና ክትትል የሚደረግላቸው 29 ሰዎች ናቸውም ተብሏል።

እስካሁን በአገራችን አጠቃላይ 186 ሺህ 985 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም