ሳውዝ ዌስት አካዳሚ ለልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕክል 200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሳውዝ ዌስት አካዳሚ ለልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕክል 200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) ሳውዝ ዌስት አካዳሚ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕክል የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
አካዳሚው ድጋፉን ያደረገው በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ሳቢያ ማዕከሉ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለማቃለል መሆኑም ታውቋል።
የሳውዝ ዌስት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ እደግልኝ ከበዶም በድጋፉ ወቅት እንደገለጹት ይህ አስቸጋሪ ጊዜ ከየትኛውም ወቅት በላይ መደጋገፍና መተጋገዝን የሚጠይቅ ነው።
በመሆኑም አካዳሚው በተለይ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ችግር ለማቃለል የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ሕፃናት በተለይም የልብ ሕሙማን ሕፃናት የተለየ እንክብካቤና እገዛ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሁሉም የተቻለውን እንዲያደርግ አቶ እደግልኝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሳውዝ ዌስት አካዳሚ ዛሬ ለማዕከሉ ያበረከተውን 200 ሺህ ብር ያሰባሰበው ከተቋሙ ሠራተኞችና ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕክል ዳይሬክተር አቶ ኅሩይ ዓሊ አካዳሚው ከዚህ ቀደም ድጋፍ ያደርግ እንደነበር አስታውሰው አሁንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላደረገው በጎ ተግባር አመስግነዋል።
ሌሎች ተቋማትም የሳውዝ ዌስት አካዳሚን መልካም አርአያ በመከተል የልብ ታማሚ ሕፃናትን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕክል የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ የገጠመው የንዘብ ችግር እየተባባሰ መምጣቱንም አስረድተዋል።
ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከመከሰቱ በፊት ማዕከሉ በወር እስከ አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ ያገኝ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኅሩይ አሁን ላይ ግን በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በሰዎች እንቅስቃሴ ላይም ችግር በመፍጠሩ ወደ ማዕከሉ ለሕክምና የሚመጡት በአንጻራዊነት መቀነሳቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህ ወቅት የልብ ሕሙማን በኮቪድ -19 በእጅጉ ከሚቸገሩ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደም በመሆናቸው በማዕከሉ የሕክምና አገልግሎቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ኅሩይ ገልጸዋል።
የማዕከሉ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የግለሰቦች፣ የማኅበረሰቡ፣ የተቋማትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ እንዳይለያቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕክል በአዲስ አበባ ከተቋቋመ 31 ዓመታትን አስቆጥሯል።