ምክር ቤቱ በሦስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በሦስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2012(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 85ኛ ስብሰባ ረቂቅ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂና የኮር ቤቲ የኃይል ግዢ ስምምነትን ጨምሮ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አፀደቀ።
ውሳኔዎቹን የጸደቁት ዛሬ ጠዋት ከተወያየባቸው በኋላ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ያጸደቃቸው ከኮርቤቲ ጋር የሚደረገው የኃይል ግዢ ስምምነት፣ ረቂቅ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራተጂና የማዕድን ሥራዎች ዓዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ዓዋጅ እንዲሁም ሁለተኛው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ናቸው፡፡
ከኮር ቤቲ ጋር የሚደረገው የኃይል ግዢ ስምምነት መንግሥት ረጅም ጊዜ የጠየቀ ዝግጅት ካደረገ በኋላ መጠናቀቁ ተገልጿል።
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚከወንን የጥምረት ሥራ፣ የውጪ አካላት በቀጥታ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱበትን የእንፋሎት ኃይልና የኢነርጂ ዓዋጆችን፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያካሂድባቸውን ሁኔታዎችን አጥንቶ ማጽደቅ የዚሁ ሥራ አንድ አካል እንደነበር አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በአንድ በኩል እንዲሁም የኮርቤቲ ና ቱሉ ሞዬ ኩባንያዎች ደግሞ በሌላ በኩል በመሆን በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚካሄደውን ጥምረት በመከወን በአጠቃላይ 300 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ኃይል እንደሚያመነጩም ገልጿል።
የኢትዮጵያ እንፋሎት ኃይል ዘርፍና ተያያዥ ክህሎቶች፣ የኢትዮጵያን የኃይል ዐቅም፣ ዋስትና እንዲሁም አስተማማኝነት በሚያረጋግጥ መልኩ አረንጓዴ፣ ንጹሕ እና ታዳሽ የኃይል ምንጭ በጥቅም ላይ እንደሚውል አስረድቷዕ፡፡
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ መንግሥት የፈጠራ ሥራዎችና ዲጂታል አገልግሎት በማስፋፋት ሁሉን አካታች ዕድገት ለማምጣት የሚያከናው ነው ሥራ ማዕከል መሆኑም ተጠቁሟል።
ቀበሌዎች ከወረዳዎች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከርም ዲጂታል ዕውቀትን ለማሳደግ፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግና በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማዳበር መታለሙንም አስታውቋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚውን በፍጥነት ለማሳደግ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የንግድ አሠራር በሚያዘምን መንገድ፥የመንግሥት አካላት ዲጂታል አገልግሎትን በውጤታማነት ለማቅረብ ያግዛል ብሏል።
ይህም መንግሥት የንግድ ሥራዎች በተቀላጠፈ መንገድ ለማካሄድ የተገበራቸው ተከታታይ ማሻሻያዎች አካል መሆኑን መግለጫው አስረድቷል።
የንግድ ሕጉ ነባሩ የንግድ ሕግ ከጸደቀ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ መጽደቁን ያስታወሰው መግለጫው፤ የሕግ ሥርዓቱን ለማዘመን በሚደረገው ሂደት ውስጥ አንድ ምዕራፍ መሆኑንም አመልክቷል።
አዲሱ የንግድ ህግ መንግሥት የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመገንባት ያለውን ፍላጎት ባማከለ መልኩ የፈጠራና የንግድ ሥራዎች ክንውንን እንደሚያነሳሳም ገልጿል።
ምክር ቤቱ የማዕድን ሥራዎች ዓዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ዓዋጅ ላይም ተወያይቶ ረቂቅ ዓዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምዕ አጽድቋል፡፡