ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች 12ሺህ 877 ተማሪዎችን አስመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች 12ሺህ 877 ተማሪዎችን አስመረቁ
አምቦ/ጎባ/ሶዶ ሰኔ 30/2010 የአምቦ፣መዳወላቡና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር በቅድመና ድህረ ምረቃ ያሰለጠኗቸውን 12ሺህ 907 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቁ ። በቀሰሙት እውቀት ህዝቡን በቅንነት በማገልገል በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂዎች ገልፀዋል ። በተለይም የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካሰመረቃቸው 5ሺህ 300 ተማሪዎች ውስጥ 1ሺህ 322ቱ ሴቶች ናቸው ። ዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ሰጥተዋል ። ዶክተር ቶላ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት "ተመራቂዎች በተሰማሩበት መስክ ህዝቡን በቅንነት በማገልገል ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ የማስቀጠል ሀላፊነት ተጥሎባችኋል " ብለዋል ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የተጣለበትን ሀላፊነት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ። ከእለቱ ተመራቂዎች መካከል 3 ነጥብ 99 በማምጣት የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ዶአሎ አባገኘ "በቀሰምኩት እውቀት ህብረተሰብን በአግባቡ በማገልገል በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ተዘጋጅቻለሁ " ብሏል ። በተመሳሳይ የማዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 3ሺህ 455 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል ። ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች ውስጥ 38ቱ በህክምና ዶክተርነት የሰለጠኑ ናቸው ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተካ በወቅቱ እንደገለፁት ምሩቃን በተቋሙ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ትግባር በመቀየር አገሪቷን ከድህነትና ከኋላቀርነት ሊያላቅቁ ይገባል ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የዘንድሮውን ምረቃ ልዩ የሚያደርገው መንግስት በትምህርት ተደራሽነት ላይ የተቀዳጀውን ስኬት በጥራት ላይ ለመድገም የትምህርት ጥራት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እየተሰራ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተያዘውን ግብ ለማሳካት ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የጥናት፣ ምርምርና የተጠናከራ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን እውን ለማድረግ አሳታፊ የሆነ እቅድን በማዘጋጀት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ። የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎች የሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማት ሰጥተዋል ። ተመራቂዎች በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚጠበቅባችውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ። በቢዝነስ አስተዳደር በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀው ፋዲል አልይ በበኩሉ “አገሪቱ አዲስ የለውጥ ተስፋ የሰነቀችበት ወቅት በመሆኑ በተመረኩበት መስክ ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል ሀገራዊ የለውጥ ጉዞውን ለማስቀጠል የድርሻየን እወጣለሁ " ብሏል ። ዩኒቨርሲቲው የእለቱን ተመራቂዎች ሳይጨምር ከ2001 ዓ. ም ጀምሮ 19 ሺህ 126 ተማሪዎችን ማስመረቁ ታውቋል። በንድፈ ሃሳብና በተግባር የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ በሃገሪቱ የለውጥና የዕድገት ጉዞ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የገለፁት ደገሞ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲርቲ ምሩቃን ተማሪዎች ናቸው ። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስረቃቸው 4ሺህ 152 ተማሪዎች መካከል 1ሺ569 ሴቶች ናቸው፡፡ ከእለቱ ምሩቃን መካከል በባዮሎጂ የትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 97 በማምጣት ተሸላሚ የሆነችዉ ኤልሳ ተስፋዬ በነበራት ቆይታ ብዙ ችግሮች ቢገጥማትም በጥንካሬ ለጥሩ ውጤት በቅታለች፡፡ “በዩኒቨርሲቲው ቆይታየ ያገኘሁችሁን ዕውቀት በመጠቀም ሃገሬንና ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ “ ብላለች ። የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥና አንድነት ለማስቀጠል የድርሻዋል ለመወጣት መዘጋጀቷን አረጋግጣለች ። የዩኒቨረሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተመራቂዎች ራሳቸውን ለማብቃትና ሙያቸውን ለማሻሻል ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባልና የእለቱ ክብር እንግዳ ዶክተር ንጉሤ ዳና በበኩላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥና የሽግግር እቅዶችን መፈጸም የሚችል የተማረ ሃይል ለማፍራት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ተመራቂዎች በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በዕውቀት በመምራት በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ የሃገሪቱን ዕድገት ዘላቂ ማድረግ እንደሚኖርባቸው መልእክት አስተላልፈዋል ። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ሰአት በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር በቅድመና ድህረ ምረቃ ከ54 በሚበልጡ የትምህርት አይነቶች ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ታውቋል ።