ቀጥታ፡

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት ከጀርሞች እንዳይላመዱ ጥንቃቄና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል... ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2012(ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኃኒት በጀርሞች እንዳይላመዱ ጥንቃቄና ቁጥጥር እንዲደረግ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

ሚኒስትሯ ማሳሰቢያውን የሰጡት የፀረ-ተህዋሲያን ብግርነት መቆጣጠርና መከላከል ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ቀኑ "የፀረ-ተህዋሲያን ብግርነት መቆጣጠርና መከላከል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት" በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ለስምንተኛ ጊዜ ተከብሯል።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ዓለማችንን ከሚያሰጓት የጤና ችግሮች አንዱ መሆኑን በዚህ ወቅት ተገልጿል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ ችግር የሚሞቱ ሲሆን፤በተለይ እንደ ቲቢ፣ ወባ፣ኤች አይቪ /ኤድስ ባሉ በሽታዎች በስፋት የሚጠቁት ታዳጊ አገሮች ደግሞ የችግሩ ዋነኛዎቹ ገፈት ቀማሾች ናቸው።

ዶክተር ሊያ  በዚሀ ጊዜ እንዳሳሰቡት የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ የሰው ሕይወትን ከመቅጠፉ ባሻገር፤ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ጫና ያስከትላል።

የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ግለሰብ የጸረ ተህዋሲያን መድኃኒትን ለሚፈልጉ ኢንፌክሽኖች የመጋለጡ ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህን ወቅት ጥንቃቄ ካልተደረገ መድኃኒት ጀርሞች እንዲላመዷቸው በማድረግ አሳሳቢ የጤና እክል ያስከትላል በማለት፤

መድኃኒቱ በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ ሊወሰዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምርት ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ በበኩላቸው የጸረ ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት እንሚጠይቅ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ይህን በመረዳት ችግሩን ለመከላከል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መንደፉንም ተናግረዋል።

ስትራቴጂው የተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ የሚሳተፉበት ስልት መቀመጡንም አስታውቀዋል።

የጸረ ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድና የኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ መስፍን ጉጂ ናቸው።

 "ሁለቱንም የጤና ችግሮች አስቀድመን መከላከል ካልቻልን በመድኃኒት ሕክምና የማዳኑ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ" ብለዋል።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የጸረ ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ ላይ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ እንደ አውሮፓውያን  አቆጣጠር እስከ 2050 ባለው ጊዜ ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው ያልፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም