ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል-- አምባሳደር መለሰ ዓለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል-- አምባሳደር መለሰ ዓለም
ሰኔ 8/2012( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ሀገር በመሆኗ ተጨማሪ ወደቦች እንደሚያስፈልጓት በኬኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።
ኢትዮጵያ የላሙ ፕሮጀክት መጠናቀቅን በጉጉት እየጠበቀች መሆኑንም አምባሳደር መለስ አስረድተዋል።
አምባሳደር መለስ አያይዘውም የላፕሴት ኮሪደር ለደቡባዊ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
የጅቡቲ፣ የሱዳንና የኤርትራ ወደቦችን መጠቀም ለደቡባዊ የኢትዮዽያ ክፍሎች ካላቸው ርቀት አኳያ አዋጭ አለመሆኑንም አምባሳደር መለስ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደቡን የምትፈልገው ኬኒያን ለማስደሰት ሳይሆን ለራሷ ጥቅም ብላ መሆኑን አምባሳደሩ መናገራቸውን በኬኒያ የሚታተመው ዘስታር ዘግቧል።
የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የወደብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ እስኪገባ በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን አምባሳደር መለስ አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በኬኒያ ያላቸው የሥራ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ሥራ እንዲጀምር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው ሦስቱ አገራት ሥራው በቶሎ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ የሁለተኛ ምዕራፍ ሥራዎች ምሥራቅ አፍሪካን ከምዕራብ አፍሪካ ወደቦች ጋር የሚያገናኙ የመንገድ ሥራዎች ይኖሩታል ብለዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ የፕሮጀክቱ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በጋራ መጎብኘታቸውን ጋዜጣው አስታውሷል።
ፕሮጀክቱን በጋራ የሚያስኬዱት ኬኒያ፣ ኢትዮጵያና ደቡቡ ሱዳን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሥምምነት ማድረጋቸውን ጨምሮ አመልክቷል።
እኤአ በ2012 በቀድሞዎቹ የኢትዮዽያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በኬንያው ፕሬዝዳንት ሙዋይ ኪባኪ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ሀሳብ አመንጪነት ተጀምሮ በገንዘብ እጥረትና በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት ምክንያት ሊጠናቀቅ አለመቻሉን ጋዜጣው አስታውሷል።
አሁን የፕሮጀክቱን ሥራ ለማፋጠን ሲባልም ከኬኒያ ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን መረጃው አስታውሷል።
ፕሮጀክቱ ላሙ ወደብ ላይ 32 መርከቦችን ማቆም የሚያስችልና የነዳጅ ዘይት ማጣሪያና አውሮፕላን ማረፊያዎችን ያካተተ መሆኑን ጋዜጣው አስረድቷል።
ገቢና ወጪ የንግድ ሥራዎችን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ ቅንጡ ሆቴሎችን የያዙ አነስተኛ ከተሞችንም እንዳካተተ ዘገባው አስታውሷል።