ቀጥታ፡

በአፋር ክልል አውሲ ረሱ ዞን ለተቸገሩ 200 ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

አፋር፣ ሰኔ 08/2012 (ኢዜአ)  በአፋር ክልል አውሲ ረሱ ዞን ጭፍራ ወረዳ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 200 ወገኖች የአንድ ወር ምግብ ድጋፍ ተደረገላቸው።

ድጋፍ የተደረገላቸው  ኤች አይ ቪ ኤድስ  በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖችን ጨምር እንደሆነ ተመልክቷል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የክልሉ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መዲና ማህሙድ  ድጋፉ በተደረገበት ወቅትም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝባቸው  ወገኖች ለኮሮና  ግንባር ቀደም ተጋላጭ ናቸው።

ይህንን ለመከላከል  ጽህፈት ቤቱ በአይሳኢታ፣ ዱብቲና ሎግያ ከተሞች የገንዘብና የንጽህና መጠበቂያ  ድጋፍ  እያደረገ ነው ብለዋል።

ችግሩን በመንግስት ውስን በጀት ብቻ መቋቋምም ሆነ የተቸገሩ ወገኖችን የበሽታው ተጋላጭነት መቀነስ ስለሚያዳግት የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል።

ቫይረሱን ለመከላከልና የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ ጭፍራን  ጨምሮ በተወሰኑ ወረዳዎች የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ በማድረግ ያሳዩት ዝግጁነት ሌሎችም ሊፈጽሙ  እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጭፍራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ አቶ ውቲካ ኖሬ በበኩላቸው በወረዳው ከሰራተኞችና ባለሃብቶች ባገኙት ድጋፍ 200 ለሚሆኑ አቅመ-ደካሞችና ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ለሚገኝባቸው ወገኖች  የአንድ ወር ቀለብ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ይህም  ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደሚገመት አመልክተው  በነፍስ ወከፍም  25 ኪሎ ግራም  ዱቄት ፣  25 ኪሎ ግራም ሩዝ ፣ አምስት ሊትር የምግብ ዘይትና  አምስት  ኪሎ ግራም ስኳር ማከፋፈላቸውን ገልጸዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በወረዳው  ብርሃን የኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ማህበር መስራች አቶ ነጂብ መሃመድ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊትም በጎ-ፈቃደኛ ወጣቶች ለ39   አባላት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ  ወረዳው ያደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን  ለማቃለል እንደሚያግዛቸው  በመግለጽ ምስጋና  አቅርበዋል።

ወይዘሮ ለይላ መሃመድ በበኩላቸው በሰው ቤት እየሰሩ  በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ልጆቻቸውን ለማሳደግ  ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት ስራው በመቆሙ ያጋጠማቸውን ችግር ለማቃለል አሁን የተሰጣቸው ድጋፍ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በአፋር ክልል  ከ14ሺህ በላይ ወገኖች ኤች አይ ቪ ኤድስ  በደማቸው እንደሚገኝባቸው የክልሉ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም