ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ከኮሮና መከላከል ጎን ለጎን ለመደበኛ ህክምና ትኩረት መሰጠት አለበት ... የጤና ሚኒስትር

ድሬዳዋ ሰኔ7/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ኮሮናን ለመከላከል የሚከናወኑ አበረታች ጥረቶችን በማጠናከር መደበኛ የህክምና አገልግሎቱን በትኩረት እንዲሰራ የጤና ሚኒስትር ደኤታ አሳሰቡ ።

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራ ቡድን በድሬዳዋ ተገኝቶ ኮሮናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ተግባራትን የተመለከተ ሲሆን ከአመራሩ ጋርም ተወያይቷል፡፡

በዚሁ ጊዜ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለፁት ኮሮናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ።

በድሬዳዋ ችግሩ በተከሰተበት ወቅት የመከላከሉ ሂደት የተበታተነና ሥርዓት ያልያዘ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን  በአመራሩና በባለሙያዎች የተፈጠረው ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በኮቪድ 19 የሳቢያን ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ የሚታየው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ዘመናዊ የፈጠራ ውጤቶች በሥራ ላይ በማዋል፣ የጤና ግብአቶችን ከብክነት በማዳንና የቤት ለቤት የልየታ ተግባራት በማከናወን አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀመ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።

በተጨማሪ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከአስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት እያከናወነ የሚገኘው ሥራ አበረታች ነው ።

እንደ ዶክተር ደረጃ ገለፃ በቀጣይ ጊዜያት የቫይረሱ ስርጭት ሊጨምር ስለሚችል ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ከማድረግ ጎን ለጎን የመደበኛ ህክምና አገልግሎትንም መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ዝግጅትና ምላሽ ግብረ ኃይል የክልሎች አስተባባሪ ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት በድሬዳዋ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አመራሩና ባለሙያዎች ተቀናጅተው የሠሩት ተግባራት የሚበረታታና ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡

ጅምሩን በማጠናክር የምርመራ ስራውን ማስፋት አስፈለጊ መሆኑንም ተናግረዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮና ጤና ተቋማት መደበኛ የህክምና አገልግሎቶች በተገቢው መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የበለጠ ጠንክረው መስራት አለባቸው ።

በጤና ሚኒስቴር የተመራው ቡድን ድሬዳዋ ተገኝቶ ሥራዎችን መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡ ወደፊት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ያግዛል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው፡፡

የተነሱ ጥንካሬዎች በማጎልበትና ክፍተቶችን በመሙላት የመከላከል ስራው በተናበበ መልኩ ለመፈፀም እንሰራለን ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም