የፖለቲካ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ላሳለፈው ውሳኔ ተገዢ መሆን አለባቸው - ፕሮፌሰር በየነ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ላሳለፈው ውሳኔ ተገዢ መሆን አለባቸው - ፕሮፌሰር በየነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7/2012 ( ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ላሳለፈው ውሳኔ ተገዢ መሆን እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።
ወቅቱ ኢትዮጵያን ለገጠሟት ፈተናዎች በጋራ ሆነን መፍትሔ የምንፈልግበት ነው ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው የ5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባው 6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ማፅደቁ ይታወቃል።
ምክር ቤቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሆኖ እስካለበት ድረስ የሁሉም ምክር ቤቶች ስልጣን እንዲቀጥልም ወስኗል።
ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑን ዓለም ዓቀፍ የጤና ተቋማት ማረጋገጫ ከሰጡና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንኑ ካጸደቀ በኋላ ከ9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ምርጫ ይካሄድ ሲልም የውሳኔ ሃሳቡን አጽድቋል።
ኢዜአ በዚህ የምክር ቤቱ ውሳኔ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን አነጋግሯል።
ፕሮፌሰሩ ምክር ቤቱ ሕገ-መንግስቱ በምርጫ መራዘም አለመራዘም ግልጽ ያልሆነ ነገር ባለማስቀመጡ ምክንያት የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ምርጫውን ማራዘሙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ያማከለ ነው ብለዋል።
ፓርቲያቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚያከብርና ከመንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔውን ማክበር እንደሚገባቸውና ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ማተኮር የሚገባው ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጪም ያሉባትን ፈተናዎች በጋራ መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሆነም አመልክተዋል።
በመንግስት በኩል 'አሁን በተገኘው የእፎይታ ጊዜ ለችግሮች በጋራ መፍትሔ እናብጅ' በሚል ለቀረበው ጥሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጎላ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለገጠሟት ወቅታዊ ፈተናዎች መፍትሄ የማበጀት ተግባር የመንግስት ብቻ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።