ተጨማሪ 179 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ2 ሰዎችም ሕይወት አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ተጨማሪ 179 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ2 ሰዎችም ሕይወት አልፏል
ሰኔ7/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4845 የላብራቶሪ ምርመራ 179 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ2 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3ሺህ 345 ደርሷል፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 176 ሰዎች ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ 3ቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ሲሆኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 116 ወንድና 63 ሴት እንዲሁም የዕድሜ ክልላቸው ከ2 ወር ህጻን እስክ 80 አመት እንደሆነ ታውቋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 111 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ 15 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 11 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 9 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 5 ሰዎች ከሱማሌ ክልል፣ 2 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ 23 ሰዎች ከአማራ ክልል ፣ 1 ሰው ከሀረሪ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የ 2 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ሁሉም በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆናቸው ታውቋል።
በዚህም አጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 57ደርሷል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።
በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት 50 ሰዎች ( 41 ከአዲስ አበባ፣ 3 ከአፋር፣ 2 ሰዎች ከትግራይ ከሱማሌ ና 4 ከአማራ ክልል ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 445 መድረሱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በጽኑ ህክምና ክትትል የሚደረግላቸው 30 ሰዎች ናቸውም ተብሏል።
እስካሁን በአገራችን አጠቃላይ 181 ሺህ 349 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።