ቀጥታ፡

ፓርቲዎች የጋራ መግባባት በሚፈልጉ አጀንዳዎች ላይ በትብብር አለመስራታቸው የኢትዮጵያን እድገት ወደ ኋላ ጎትቷል

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2012(ኢዜአ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ በትብብር አለመስራታቸው የኢትዮጵያን እድገት ወደ ኋላ እንደጎተተ ተገለጸ።

በአሁኑ ወቅት በጋራ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትብብር ለመስራት ፓርቲዎች የሚያሳዩት አቋም ጅምሩ መልካም መሆኑም ተገልጿል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሆነው ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር አካሂደዋል።

የብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ዛሬ ማለዳ በየካ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሚሌኒየም ፓርክ ችግኝ ተክለዋል።

የዛሬው የችግኝ ተከላ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ለመትከል የታቀደው የሰባት ሚሊዮን ችግኝ ተከላ እቅድ አካል ነው።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ በትብብር አለመስራታቸው የኢትዮጵያን እድገት ወደ ኋላ መጎተቱን ገልጸዋል።

ይሁንና በአሁኑ ሰአት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በትብብር ለመስራት እያሳዩት ያለው አቋምም ጅምሩ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን የመቋቋምና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ለአንድ አካል የሚተው ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ላይ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ''የተፎካካሪ ፓርቲዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፎ ማድረግ በሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች በትብብር የመስራት መንፈስን ያጠናክራል'' ብለዋል።

በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመስራት ባህል ሊጎለብት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በአረንጓዴ አሻራ ላይ የታየው ትብብር በሌሎች አገራዊ አጀንዳዎችም ላይ ሊደገም እንደሚገባው ገልጸዋል።

በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተተከሉ ችግኞችን በዘላቂነት በመንከባከብ ለአረንጓዴ አሻራ ስራው መሳካት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አቶ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

በመርሃ ግብሩም በመላ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም