በሰሜን ሽዋ ዞን በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የአስፓልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሽዋ ዞን በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የአስፓልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2012(ኢዜአ)በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ የ108 ኪሎሜትር አስፓልት መንገድ ስራ ተጀምሯል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የመንገዱ መገንባት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታላቸው ገልፀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በደብረብርሃን እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ ጉብኝታቸውን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከሚያስተምረው ኃይሌ ሚናስ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር የጀመሩት።
የደብረ ብርሃን ቴርሸሪ ሆስፒታል፣ የአንኮበር መንገድና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችም ተጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደብረ ብርሃን-ጅሁር-ደነባ ለሚገነባው የ108 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይም አስቀምጠዋል።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም የመንገዱ መገንባት የአርሶ አደሩን የሰብልና እንስሳት ሃብት በቀላሉ ወደ ገበያ በማውጣት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአንድ ዓመት በፊት በአካባቢው ተገኝተው በገቡት ቃል መሰረት ለዘመናት የዘለቀው የኅብረተሰቡ የመንገድ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱንም አውስተዋል።
አካባቢው በተለይ በስንዴ ምርት የሚታወቅ በመሆኑ አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት በኩል በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በብልፅግና ጉዞ የልማት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ እንደሚሄዱ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የተጀመረውን ልማት እንዳያደናቅፍና ጉዞው እንዳይገታ ሁሉም ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጪው ሐምሌ ውሃ የሚይዝበት ደረጃ ላይ በመድረሱ አርሶ አደሩ ድጋፉን እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስም የአገሪቷ የ10 ዓመታት የብልፅግና ፍኖተ ካርታ ትኩረት የመንገድ አውታርን ትርጉም ባለው ሁኔታ ማካሄድ እንደሆነ ገልጸዋል።
የመንገዱ መገንባት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተደምረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ትራንስፖርት እንዲያገኝ፤ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችም እንዲስፋፉ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ መጀመር የተገቡ ቃሎች እንደሚፈጸሙ ማሳያ ነው ብለዋል።
የመንገዱ ግንባታ እውን የሚሆነው ሲጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው ለዚሁ በሚያስፈልጉ ከወሰን ማስከበር ጀምሮ ባሉ ሂደቶች የአካባቢው ኅብረተሰብ ድጋፍ እነዲያደርግም ጠይቀዋል።
መንገዱ በአራት ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የገለጹት ደግሞ ግንባታውን የሚከውነው የሰንሻይን ኮንስትራክሽ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ታደሰ ናቸው።
የአካባቢው አርሶ አደሮችም የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው የነበረው መንገድ መገንባት ምርቶቻቸውን ገበያ ለማውጣት የነበረባቸውን አላስፈላጊ ወጪ እንደሚያስቀርላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።
መንገዱ አምስት የአማራና አንድ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎችን እንደሚያገናኝ ተነግሯል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የበግ እና የጋቢ ስጦታ አበርክተዋል።