በላይ አርማጭሆ ወረዳ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ የልማት ስራዎች በመካሔድ ላይ ናቸው

ጎንደር፣ ሰኔ 7/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ገለፁ ።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደተናገሩት የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ በትምህርት ፣ በጤናና በመንገድ ልማት ዘርፍ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡

በአካባቢው ባለፉት ሶስት አመታት በአካባቢው በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሰሩ ታቅደው የነበሩና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተስተጓጉለው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ በማከናወን  አካባቢውን ወደ ተረጋጋ ሰላም በመመለሱ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለማሟላት ወደ ተግባራዊ ስራዎች መገባቱን አስረድተዋል ።

ከልማት ስራዎቹ መካከልም በትክል ድንጋይ ከተማ በ10 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ግንባታው ተጀምሮ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ማጠናቀቅ የተቻለ ሲሆን በመጪው አመት ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ፡፡

በከተማው የሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያጋጠመውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለማቃለል 10 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተጀምሮ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በርስ የሚያገናኝ የ5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ስራ የተከናወነ ሲሆን ከትክል ድንጋይ ሮቢት ከተማ የሚያደርስው ነባር የጠጠር መንገድም ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

የሮቢት ጤና ጣቢያን ደረጃ ለማሻሻል በተያዘው እቅድ መሰረት በ5 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስችል ከስራ ተቋራጭ ጋር ውል መፈፀሙን አብራርተዋል፡፡

የወረዳው የአስተዳደር ህንጻም በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት ከ50 በመቶ በላይ ግንባታው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወረዳ መስተዳድሩ ከአመታዊ በጀቱ 60 በመቶ የሚሆነውን ለልማት ስራ እየመደበ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ህዝቡ በዚህ አመት ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ምንም አይነት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ባለመኖሩ ልጆቻችንን ጎንደር ከተማ ድረስ በመላክ ለማስተማር ተገደን ቆይተናል ያሉት የትክል ድንጋይ ከተማ ነዋሪ አቶ በዛብህ ንጉሴ ናቸው፡፡

በወረዳው የጃኒካው ቀበሌ ነዋሪ አቶ መስፍን አየነው በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በወረዳው የሰፈነው ሰላም ዳግም በአካባቢያችን ልማትና እድገት ላይ እንድንሳተፍ ቁጭትና መነሳሳት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡

የወረዳው ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት በ8 ሚሊዮን ብር ወጪ የ13 ኪሎ ሜትርየጠጠር መንገድ አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም