በሴቶችና ህጻናት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል አመለካከት ላይ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶችና ህጻናት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል አመለካከት ላይ መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2012(ኢዜአ) በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቀነስና ለመከላከል በህብረተሰቡ አመለካከት ላይ በስፋት መሰራት እንደሚገባ የሲቪክ ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በሴቶች ጉዳይ ከሚሰሩ ሲቪክ ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።
ወይይቱ በዋናነት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ጥቃቱ ሲፈጸም ምን አይነት ምላሽ መስጠት ይገባል በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ነው የተካሄደው።
በውይይቱ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በጋራ ያስጠኑት ጥናት ቀርቧል።
በጥናቱም ከመጋቢት 1 ቀን 2012 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በኢትዮጵያ 280 ሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
ጥናቱን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ጥቃት ከተፈጸመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል 273ቱ ሴቶች፤ ሰባቱ ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶችና ህጻናት መካከል 217ቱ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሲሆኑ 63ቱ ደግሞ ከ18 ዓመት በላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቀነስና ለመከላከል ህብረተሰቡ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ለዚህም በሴቶችና ህጻናትን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ በትምህርትና ፖሊሲው ላይ ከማካተት ባለፈ በህብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
እንደዚህ አይነት እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትንም በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸውና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
ጥቃት ተፈጽሞባቸው በፍትህና እንክብካቤ ማዕከላት ለሚገኙ ሴቶችና ህጻናት የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን ማሟላት ይገባል።
ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጥቃት ከደረሰባቸው 280 ሴቶችና ህፃናት መካከል 215ቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ነዋሪ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚኖሩ ተመልክቷል።
በጥናቱ እንደተመለከተው በዚህ ጊዜ ውስጥ በሴቶችና ህጻናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች የአስገድዶ መድፈርና ሙከራ፣ ግብረሰዶም እና ያለዕድሜ ጋብቻ ናቸው።