ቀጥታ፡

የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጂንሲዎች ፌዴሬሽን በችግር ሳቢያ ከውጭ ወደ አገራቸው ለተመለሱ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጂንሲዎች ፌዴሬሽን በችግር ምክንያት ከውጭ ወደ አገራቸው ለተመለሱና በለይቶ ማቆያ ለሚገኙ ዜጎች የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የተደረገውን ድጋፍ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተገኙበት በዛሬው እለት አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በህገ ወጥ መልኩ የሄዱና በተለያየ ችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ ይገኛል።

ከውጭ ተመላሾች የኮቪድ 19 ምርመራ ለማድረግ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ የመቀመጥ ግደታ ያለባቸው ሲሆን፤ ከተመላሾቹ አንዳንዶቹ የረባ ልብስ እንኳ የሌላቸው በመሆናቸው ለችግር ይዳረጋሉ።

እነዚህን ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለመርዳት በማሰብ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ስምሪት አገናሽ ኤጂንሲ ፌደሬሽን አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለግሷል።

ድጋፉ ሲደረግ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ነቢል መሐመድ እንዳሉት ህጋዊ የሆነ አካሄድ እያለ ዜጎች ህገወጥ የሆነ ጉዞ ምርጫ በማድረጋቸው በርካታ ችግሮች ይፈራረቁባቸዋል።

በተለይ አሁን ላይ በኮቪድ 19 ሳቢያ ከተለያዩ አገሮች ወደ አገራቸው መንግስት እንዲመለሱ እያደረገ በመሆኑ ፌዴሬሽኑም የተቻለውን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ዛሬ ያደረገው ድጋፍም ከ80 ኤጀንሲዎች ባሰባሰበው ከ600 ሺህ ብር በላይ የሸመታቸውን አልባሳትና የንፅህና ቁሳቁሶች መሆኑን አብራርተዋል።

ሌሎች ኤጂንሲዎችም ይህንን በጎ አርአያ በመከተል በቀጣይ ድጋፍ እንዲያደረጉ አቶ ነቢል ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ800 በላይ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጂንሲዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ፤ መሰል ድጋፎች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም