ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተቋቋመ

ባሕርዳር፣ ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ)  በአማራ ክልል ኮሮና ቫይረስን በተሻለ አቅም ለመከላከል በሦስት ከተሞች የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

ማዕከላቱን በማቋቋም ዙሪያ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ወቅት የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንደገለጹት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ለውጥ እየመጣ አይደለም።

እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ቫይረሱ ከመቀነስ ይልቅ እየተስፋፋ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሽታውን ለመከላከል ከተሰራው በተሻለ ለማከናወንና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት መቋቋም የግድ መሆኑን  አስረድተዋል።

አሁን ላይ በሽታውን ለመከላከል የተቆራረጠ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ ማስተባባሪያ ማዕከላቱ በጠንካራ የቅንጅት ሥራ ወደ ተግባር ማስገባት ይገባል።

ማዕከላቱም የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ሥጋት ባለባቸው ባሕርዳር፣ መተማ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባቲ ከተማ እንዲቋቋሙ መለየታቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣዩ ሣምንት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቅሰው፤ የግብረ ኃይል አባላት መደበኛ ሥራቸውን በማከናወን ዕቅዶችንና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ላይ ብቻ ትኩረት ያደርጋሉ ብለዋል።

በሚቋቋሙት ማዕከላት የሚመደቡት አካላትም ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ግንዛቤ መፍጠር፣ ሀብት ማሰባሰብንና በየቀኑ ተጨባጭ መረጃ  ለግብረ ኃይሉ የማመቻቸት ሥራዎችን ያከናውናሉ።

ማስተባበሪያዎቹ በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን እንደሚመሩ ያመለከቱት ዶክተር ሙሉነሽ ተጠሪነታቸው ድግሞ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ይሆናል" ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን አማካሪ አቶ ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን በተወሰኑ አደረጃጀቶች ብቻ ለመከላከል አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።

በፌዴራል ደረጃ ከኮማንድ ፖስት በተጨማሪ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ተቋቁሞ መደበኛ ሥራውን ከጀመረ ሣምንታት ማስቆጠሩን ጠቅሰዋል።

የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያው በፌዴራል ደረጃ ከሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣና መደበኛ ሥራቸው ኮሮናን መከላከል ያደረጉ አመራሮችና ባለሙያዎችን የተካተቱበት መሆኑን አስረድተዋል።

አማካሪው እንዳሉት ማስተባበሪያው የኮሮና ቫይረስ እስኪጠፋ ድረስ መደበኛ ሥራቸው ስለ ቫይረሱ የተደራጀ መረጃ ማቅረብ፣ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ባለሀብቱ እንዲሁም ልማት ድርጅቶች ሀብት ማፈላለግ ነው።

የፌዴራል መንግሥት ለሚደራጁ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያዎች በገንዘብም ሆነ በሀሳብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በባሕርዳር ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባላት፣ የፌዴራል አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ተወካይና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም