የኢትዮጵያ ውሹ ሻምፒዮና ተፈፀመ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የ2010  የኢትዮጵያ ውሹ ሻምፒዮና ዛሬ ተፈፅሟል። ሻምፒዮናው ከሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ የቀድሞ የምክር ቤት አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቷል። ከማርሻል አርት ስፖርቶች አንዱ በሆነው የዉሹ ስፖርት ሻምፒዮና ላይ ከሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 273 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች በሻምፒዮናው ላይ አልተሳተፉም። ሻምፒዮናው በዉሹ አርት እንዲሁም በነጻ ፍልሚያ (ከ48 እስከ 70 ኪሎ ግራም ዘርፍ) ተከፍሎ በሁለቱም ጾታዎች ተካሂዷል። በስነ-ምግባር የታነጹ ስፖርተኞችን ማፍራትና ስፖርቱ የደረሰበትን ደረጃ መገመገም የውድድሩ ዓላማ መሆኑን የኢትዮጵያ ዉሹ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳኜ ለኢዜአ ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ የስልጠና ውጤታቸውን በውድድሩ በመለካትና በመመዘን ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ በዉሹ አርት በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። በነጻ ፍልሚያ በወንዶች ድሬዳዋ፤ በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ አሸናፊ ሆነዋል። በዚህም መሰረት በውሹ አርት አጠቃላይ አሸናፊ አዲስ አበባ ሲሆን በነጻ ፍልሚያ አጠቃላይ አሸናፊ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሆኗል። በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ውሹ የሚለው ቃል የመጣው ከቻይና  ሲሆን "ው" ማለት ወታደራዊ "ሹ" ደግሞ አርት ማለት ነው። ውሹ ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለየው እጅና እግርን እኩል በማስተባበርና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚካሄድ የስፖርት ዓይነት በመሆኑ እንደሆነ ይነገርለታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም