የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ ህዝቡ ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና መጠበቅ አለበት...አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ ህዝቡ ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና መጠበቅ አለበት...አቶ ደመቀ መኮንን
ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 6/2012(ኢዜአ) በሀገሪቱ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ ህዝቡ ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልልና የዞን ስራ ኃላፊዎች ቡድን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት መንግስት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበር ሁሉም ዜጋ ልማት ላይ እንዲያተኩር እየሰራ ነው።
ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የተጀመረውን ልማት እንዳያደናቅፍ የብልጽግናን ጉዞ ለማሳለጥ ሁሉም ህዝብ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው መጠበቅ እንዳለበት አሳሰበዋል።
በተለይም አርሶ አደሮች ከኮሮና በኋላ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተተነበየውን የምግብ እጥረት ችግር ለማስቀረት ሙሉ አቅማቸውን በሰብልና እንስሳት ልማት በማዋል ድርብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው" መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው" ብለዋል።
ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የቀመጠለት መንገድም የአርሶ አደሩን የሰብልና እንስሳት ሃብት ወደ ገበያ በቀላሉ አውጥቶ በመሸጥ የከተማውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጪው ሃምሌ ወር ውሃ የሚይዝበት ደረጃ ላይ በመድረሱ አርሶ አደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክልት አስተላልፈዋል።
የትራንስፖርት ሚንስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ከደብረ ብርሃን- ለሚ መገንጠያ- ጅሁር ደነባ የሚገነባው ከ108 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
መንግስት ከሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ መንገዱ ሲሰራ የአካባቢው ማህበረሰብ ለተቋራጩ የግንባታ ማምረቻ ቦታዎችን በመስጠትና የወሰን ማስከበር ስራውን በማቀላጠፍ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።
መንገዱም በአካባቢው የእንስሳት በማርባትና ሰብል በስፋት በማልማት ወደ ገበያ በማውጣት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
መንግስት ለዘመናት ሲንከባለል የኖረውን የዞኑን ህዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ በመመለስ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅ ናቸው።
ለዚህም ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትን ጨምሮ ሙከ ጡሪ- ለሚ- ዓለም ከተማ፤ ከዓለም ከተማ ሚዳ ደጎሎ፣ ከዓለም ከተማ አጣዬ፣ ከደብረ ብርሃን አንኮበር- አዋሽ፣ ከጣርማ በር መሃል ሜዳ በመገንባት ላይ ያሉት የመንገድ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።